አስተዳድረው የነበረው ሀገር አጅሬ የሚባል ሲሆን በቆላ ወገራ ውስጥ የሚገኝ ሥፍራ በመሆኑ ከሞላ ጐደል ዘመድ የሚበዝኀበትና ድጋፍ የማገኝበት ሀገር ስለሆነ ሁሉም ነገር በግድና በኃይል የሚፈፀም ነገር አልነበረም። ይህ አፈፃፀም ከጥንት ከአያቶቼ ተያይዞ የመጣ አሠራር ስለነበረ በእኔም ጊዜ ሁኔታው አልተለወጠም። ከእናቴ ጋር ሆነን ብዙኅ ጊዜ የምናሳልፈው ዳባት ከሚባል የደጅአዝማች አያሌው ብሩ ከተማ ስለነበረ ደጅአዝማች አያሌው ልዩ እንክብካቤ ያደርጉልን ስለነበር በአባታችን ሞት ምክንያት የጐደለ ነገር አልነበረም።
በ፲፱፻፳፯ ዓ፡ም የኢጣሊያ ጦርነት ወሬ ይነፍስ ስለነበረ በሀገሩ ባሕል መሰረት በማስተዳድረው ሀገር የሚገኘውን ተዋጊ ጦር ይዤ መዝመት እንዳለብኝ ይወራ ስለነበረ የመጣውን ጣጣ ሳላውቀው የጦር አዝማች ሆኜ የምዘምት በመሆኔ ብቻ ፈንድቄ ነበር። ስለሆነም ፤ ሁልጊዜ ከሚያስቡልን ከትልቁ ሰው ከደጅአዝማች አያሌው ብሩ እንዳልዘምት ትዕዛዝ ስለደረሰ ደስታዬን ቀጩት። የቆላ ወገራን ጦር በሙሉ ግራአዝማች ሊላይ ደሴ ፣ ኋላ ደጅአዝማች ፣ ይዘው እንዲዘምቱ ተደረገ።
ታሪክ እንደሚያስረዳን ጣሊያን የዓድዋን ድል ለመበቀል በከፍተኛ ደረጃ ተዘጋጅታ የመጣች ስለሆነ ምንም እንኳ ሕዝቡ ሽረ ላይ ከፈተኛ መተላለቅ ቢያደርግም የመርዙን ቃጠሎና መከራ ሊቋቋመው አልቻለም። ብዙኅ ሠራዊት አልቆና ቈስሎ የተረፈው በተጐሳቀለ ሁኔታ ሲመለስ ልቅሶና ጩኸቱ በየመንደሩ ይሰማ ጀመር። በመንደር ውስጥ የቈየነውም ጭንቀቱና ፍርሃቱ እጅግ አሳሰበን። በተለይ እናቴ ከባድ ጭንቅ ውስጥ ገቡ። የሚሆኑትን አጡ።
በካፕቴን የሚመራ የድል አድራጊው ጦር አጅሬ ከእኛው ባድማ ላይ መጥቶ ሠፈረና ሕዝቡ መሣሪያውን እንዲያስረክብና የሰላም ኑሮውን እንዲቀጥል አወጀ። ሕዝቡ ግን ፈፅሞ መንፈሱ ድል ያልተመታ ስለሆነ ለጦርነት በመዘጋጀት ላይ እንደነበረ መረዳት ይቻላል። ጣሊያኑ ወደ እኛይቱ መሬት ሲመጣ አስቀድሞ የሰውን ታሪክና ይዞታ በሚገባ አጥንቶ የመጣ ስለሆነ አጅሬ በሠፈረ በሳምንት ጊዜ ውስጥ እኔንና ወንድሜን ወደ ኢጣሊያው ሠፈር እንድንቀርብ በመታዘዙ እናታችንና ዘመድ ወዳጅ ሁሉ በከፍተኛ ፍርሃትና ሽብር ላይ ወደቁ። ውባዬ ለገሠ የሚያደርጉትን የሚያውቁ ብርቱ ሽማግሌ ስለነበሩ በድፍረት ይዘውን ሄዱና ተገናኘን ፈረንጁም በክብር ተቀበለን። እኛም በክብርና በምቾት ያደግን ልጆች ስለነበርን ክብራችን የተጠበቀልን ልጆች ሆነን እንዳገኘን ገመተን። ወዲያውኑ ውሎ ሳያድር የድሮ ግዛቴን ሰጥቶ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ስብከቱን ቀጠለ እኛም በደኅና ወደቤታችን በመመለሳችን ታላቅ ደስታ ሆነ።
የሀገሬው ጀግና ፣ ይህን አህያ እናሳየዋልን ፣ የሚለውን አነጋገር በመብዝኀቱ ወሬው ከኢጣሊያው ጆሮ ሳይደርስ አልቀረም። ብዙኅ ጊዜ ውባዬ ለገሠ ሳያወላውሉ ወዲያውኑ ወደ ቆላ ወገራ በረሃ ይዘውን ሸሹ። ይህ በሆነ በጥቂት ቀናት ውስጥ አርበኛው ተነሣሥቶ የኢጣሊያኑን ሠፈር ለመደብደብ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን በይፋ ይሰማ ስለነበረ ጣሊያኑ በወሬው ተሸብሮ የሰበሰበውም የጦር መሣሪያ አቃጥሎ ሸሽቶ አመለጠ። አርበኛው ግን የተቃጠለውን መሣሪያ የዋንዛ እንጨት እየጠረቡ መልሰው በመገጣጠም ጦርነቱን በይፋ ተያያዙት። እኛም ውባዬ ለገሠ ቀደም ብለው አሸሽተውን ወደ ነበረው መንደራችን ተመልሰን መኖር ጀመርን። ከላይ እንደገለጽሁት ያለንበት ሀገር ዘመድ በብዝኀት የሚገኝበት በመሆኑ ሕዝቡ ለመኖር የሚያስችለንን ነገር በሚገባ እየሰጠ ኑሯችን ሳይበላሽ መኖሩን ቀጥለናል።