ራስ ገብረመድኅን ኃይለማርያም ከወንድሞቻቸውና ከእኅቶቻቸው ለየት የሚያደርጋቸው ቍጥር ፵፭ ይደርሳል የሚባል ልጆች መውለዳቸው የዘሩን ቍጥር እጅግ በጣም ከፍ ያደርገዋል። እንግዲህ የአያቴን የወይዘሮ ጥሩነሽ ገብረመድኅን እናት ከጐጃም አምጥተው አያቴን ፊትአውራሪ ረታ ክንፉን አግብተው ወልደሥላሴ ፣ አያልነሽ ፣ ዘውዱና ፣ ዘነበች የሚባሉ አራት ልጆች ወልደዋል። የእኔ አባት ቀኝአዝማች ወልደሥላሴ ረታ እኔ የሁለት ዓመት ልጅ ሳለሁ ትንሽ ወንድሜ የአንድ ዓመት ልጅ ሳለ ሲሞቱ። ሌላው ልጅ ዘውዱ ረታ የተባለው አጐቴም በወጣትነቱ ወርኆች ስለሞተ ሴት አያቴ ከባድ ኀዘን ስለገጠማቸው በአርባ ዓመታቸው መነኰሱ። ተከታትሎም የኢጣሊያ ጦርነት መጥቶ ሀገራቸው ከመከራ ውስጥ በመግባቷ ኀዘናቸው እጅግ እየመረረ በመሄዱ ሥጋዊውን ዓለም መንነው ወደ ዋልድባ ስቋር ገዳም ገቡ።
እናቴ ወይዘሮ እጅጊቱ ተድላ መኰንን በጐንደር ክፍለ ሀገር ጋይንትና ደብረታቦር አውራጃዎች እንደሚወለዱ ጠቅሻለሁ። አባታቸው ቀኝአዝማች ተድላ መኰንን ትውልዳቸው ሙጃን ፣ ሰማዳንና ፣ በሽሎን ተሻግሮ ኮሬብን ያካትታል። ቀኝአዝማች ተድላ መኰንን በትውልዳቸው የገበሬ ቤተሰብእ ናቸው። አያታቸው ሀብቱ ገብረመድኅን በእርሻ የከበሩና የታወቁ ሰው በመሆናቸውም በላይ አርባ የሚሆኑ ልጆች የወለዱ በመሆናቸው በሀገሬው አነጋገር ዘራቸው ወሎንና ሙጃን ፣ ሰማዳን ያጥለቀለቀ በመሆኑ የሀብቱ ገብረመድኅን ዘር ድንጋይ ቢፈነቀል ይገኛል እየተባለ ስለሚነገር ከዚህ ዘር የሚወለድ ሁሉ ተጐንብሶ ውኀ ቢጠጣ አይሠጋም ይባልለታል። የእኝህ ሰው የልጅ ልጅ ተድላ መኰንን በልጅነታቸው ከእረኝነት ጠፍተው ወደ አዲስ አበባ መጥተው ለእተጌ ጣይቱ ከሥልጣን ላይ ሥልጣን እየጨመሩ ከከፍተኛ ቦታ አድርሰዋቸዋል። ቀኝአዝማች ተድላ መኰንን በዚህ አጋጣሚ ብዙኅ ሰዎችን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር ይባላል።
ሴቷ አያቴ ወይዘሮ ዘገየች ለማ ሲባሉ ትውልዳቸው በእናታቸው ጋይንት የፊትአውራሪ መረዋ የልጅ ልጅ የደጅአዝማች ብርሌ መኰንን የአክስት ልጅ ያደጉት በደጅአዝማች ብርሌ ቤት ነው። አባታቸው መጋቢ ለማ የሚባሉ የቤተልሔም መጋቢ ልጅ ናቸው። ደጅአዝማች ብርሌ ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው ሲመጡ ዘገየች ለማ አብረው ስለመጡ አዲስ አበባ ከቀኝአዝማች ተድላ መኰንን ጋር በመጋባታቸው አንዲት ሴትና አንድ ወንድ ልጅ ወልደው ቀኝአዝማች ተድላ በድንገተኛ ሕመም ታመው ስለሞቱ ወይዘሮ ዘገየች ለማ ሁለት ልጆቻቸውንና ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን ይዘው ወደ ሀገራቸው ጋይንት ሲሄዱ በየቦታው የነበረውን ርስትና አዲስ አበባ የነበራቸውን ሰፊ የከተማ ቦታ ጥለውት በመሄዳቸውና ሳይመለሱበት በመቅረታቸው ከኢጣሊያ ጦርነት በፊት በጠፍ መሬትነት ተከፋፍሏል። ወይዘሮ ዘገየች ለማ በጋይንት ፣ በሰዴ ፣ በቤተልሔም ሰፊ ርስት ስለነበራቸው ፣ የሸዋውን ርስት ዋጋ የሰጡት አይመስልም።
እንግዲህ ከላይ እንደገለጽሁት በጐንደር ክፍለ ሀገር ከገበሬው ፣ ከወታደሩ ፣ ከካህኑ ፣ ከመኳንንቱ ፣ ከመሳፍንቱና ፣ ከነገሥቱ ዘር ከሚቈጥሩ ቤተሰብእ ከመወለዴም በላይ አምስት ቅድመአያቶቼ እያንዳንዳቸው ቍጥራቸው አርባና ከአርባ በላይ ልጆች በመውለዳቸው የጐንደርም ሕዝብ የዘር ቈጣሪነት ባሕርይ ያለው ቢሆንም የጢሰኝነትና የገባርነት ታሪክ የሌለው ፣ ዘመድ ከዘመዱ የሚጣላበት ምክንያት ባለመኖሩ የዘሩን ግንድ የማወቅ ግዴታ ያለው ሕዝብ ስለሆነ ተደጋጋፊና ተቀራራቢ ሕዝብ የሚገኝበት ሀገር በመሆኑ ደጅአዝማች ከገበሬው በትውልድ ሐረጉ ልዩነት ስለማይኖረው እኵልነት የሰፈነበት ሕዝብ የሚገኝበት ሀገር ነው።
አባትና እናቴ ከመጋባታቸው በፊት ሁለቱም ጋብቻ መሥርተው ስለንበረ ፣ አባቴ አስታጥቄና ሙሉ የሚባሉ ሁለት ልጆች ሲኖራቸው እናቴ ደግሞ አልጋነሽ ፣ አሰለፈች ፣ አየለና ፣ መነን የሚባሉ አራት ልጆች ነበሯቸው። ከሁለቱ ጋብቻ የተገኘነው እኔና ደምሴ የሚባል ወንድሜ ብቻ ነበርን።
ከላይ እንደገለጽሁት አባቴ ገና ሁለት ዓመት ልጅ ሳለሁ ጠንቅቄ ሳላውቃቸው በሞት ስለተለዩኝ ያለ አባት ማደጉን ጀመርሁት። በዚያን ጊዜ በነበረው ሥርዓት መሠረት አባቴ እንደሞቱ እርሳቸው ሳሉ ይተዳደሩበት የነበረውን ሀገር እኔ በእናቴ ሞግዚትነት እንዳስተዳድር መሾሜን ካደሁ በኋላ መረዳት ቻልሁ። አስተዳደጌ እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ ትልቅ ሰው ነበር። እንክብካቤ የሚሰጡኝ ብዙኅ ዘመዶቼና የአባቴ ሰዎች ነበሩ። ትንሽ ከፍ እያልሁ ስሄድ ማንኛውም ነገር እንዳውቅና አንዳንድ ጊዜም ያላልሁትንና ያላደረግሁትን እያወሩ ያሞጋግሱኝ ነበር።