በዚህ ቦታ በእንግድነት የተቀበሉን ሰዎች ውዲያው ወደ ቤት እንደገባን ለእኔና ለወንድሜ በእርጐ የተፈተፈተ እንጀራ ሰጥተውን ስንበላ ለእናቴ ግን ለጊዜው ምንም ያላቀረቡላቸው ስለሆነ አዘንሁ። ቢሆንም ወዲያው ብዙኅ ሳይቆዩ እራት አቅርበው ከብዙኅ ጊዜ በፊት ያየነውን እንጀራ ተመገቡ። ያደርንባቸው ሰዎች በአርበኛው ክልል ናቸው ተብለው ቢቈጠሩም ወደ ኢጣሊያው ገበያ የሚሄዱ ስለሆነ በማግሥቱ ረድተው ተራራውን ወጥተን ዳባት ከተማ ደርሰን ከፊትአውራሪ ደርሶ ቤት ገባን።
የገባንበት ቤት ምግብ እንደልብ የሚበላበት ስለሆነ እስክንጠግብ በልተን በሰላም ተኝተን አደርን። በማግሥቱ ጧት ፊታ ደርሶ እኔንና ትንሽ ወንድሜን ወደ ፈረንጁ ወስደው መምጣታችንን ገለጹና ብዙኅ ተነጋገሩ። ምን እንደተነጋገሩ የምናውቀው ነገር አልነበረም። ጣሊያኑ በጣም ክፉ ዓይኑ እንደተመለከተን መረዳት ችለናል። በእኛ በኵል የቀረበው ጥያቄ ይለፍ ተሰጥቶን ወደ ጋይንት ለመሄድ እንድንችል ሲሆን ፣ ከላይ እንደገለጽሁት ከብዙኅ ንግ ግር በኋላ የተሰጠው ውሳኔ ግን ለአሥራ ኀምስት ቀን የዳባትን ዙሪያ መሬት ለእርሻ የተመቻቸ ለማድረግ በላዩ ላይ የሚገኘውን ድንጋይ የሚለቅም በብዙኅ ሺህ የሚቈጠር ሠራተኛ ተሠማርቶ ይለቅም ስለነበር ፣ እኔና ትንሽ ወንድሜ ወደዚህ ቦታ እየሄድን እንድንሸቅል ተወስኖ ተነገረን። ፊትአውራሪ ደርሶ በሁኔታው ያዘኑ ቢመስልም ከዚህ የተሻለ መፍትሔ የሚገኝ አልመሰለኝም። በመሠረቱ ሥራ ሠርተን የማናውቅ ከዚህ በላይ በደረሰብን ረሐብ ሰውነታችን በጣም የተጐዳ ስለነበረ የተመለከተን ሰው ሁሉ ያዝንልን ነበር። ቢሆንም በማግሥቱ ጧት ወደ ምንሸቅልበት ቦታ ሰዎች ወስደው አስረከቡን። ሁኔታው ለእኛ ምንም የሰጠን ስሜት አልነበረም። ይልቁንም ለሸቀል የተሰማራንበት ድንጋይ የመልቀሙ ሥራ እንደኳስ ጨዋታ የቈጠርነው ከመሆኑም በላይ በየቀኑ ዓይተነው የማናውቀውን ትልልቅ ዳቦ ይሰጡን ስለነበረ የተራበውን ሰውነታችን በፍጥነት ያድብረው ጀመር። ማታ ወደ ቤታችን ስንሄድ ተዘጋጅቶ የሚቈየንን ያማረ ምግብ መብላት ያቅተን ጀመር። እናታችንም ሁኔታውን በትክክል ባለመረዳት ከልባቸው ያዝኑና ይጨነቁ ነበር።
ወደ ሮሜ እንድንሄድ የጋበዘንን ልጆች የኢጣልያው ገዢ አዋርዶ በተሾምንበትና በተሸለምንበት በተዝናናንበት የዳባት ከተማ በሸቀላይነት አሥራ ኀምስት ቀን ከቈየን በኋላ ወደ ጋይንት እንድናልፍ ፈቃድ ተሰጠን። ፈቃዱን ባገኘን ማግሥት በጦርና በታንክ እየታጀበ በሚጓዘው በአንዱ ትሬንታ ኳትሮ ላይ ተጭነን ጕዟችንን ወደ ጐንደር ቀጠልን። ቀኑን ስንጓዝ ውለን ጐንደር የደረስነው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ስለነበረ ከተማይቱ በኤሌክትሪክ ብርሃን በቋያ እሳት የምትቃጠል መስላ ስንመለከታት ትልቅ ፍርሃትና ሽብር ተሰማን። ዘመድ ፈልገን ለማግኘትም ከሚኪናው ወርደን በእግራችን ጕዞ ጀመርን። ወደ ፒያሳው አካባቢ ስንደርስ አንድያውን ከተቃጠለ መሬት ላይ የቆምን መሰለን። ከብዙኅ ፍርሃትና ጭንቀት በኋላ ወደ አራዳው አካባቢ የምንፈልገውን አድራሻ አግኝተን ሠፈርን። ጐንደር ብዙኅ ሳንቆይ በትሬንታ ኳትሮ ተሳፍረን ደብረ ታቦር ደረስን። ከዚያም ደጅአዝማች አድማሱ ብሩ ግቢ ገብተን አደርን። የእናታችንን ዘመዶች በብዝኀት ማግኘት ስለጀመርን ችግራችንና ፍርሃታችንም እየቀነሰ መጣ። ደብረ ታቦር በየቦታው እየተጋበዝን የነበርንበትን የረሐብ ሀገር የረሳነው መሰለን። ከዚህም ብዙኅ ሳንቆይ ጕዟችንን ቀጥለን ነፋስ መውጫ ደረስን። በዚህ ከተማ ትንሽ ካረፍን በኋላ ወጣ ብሎ የደሮ ከሚባለው መንደር የእናቴ ወንድም የግራአዝማች ወንድአውክ ተድላ ቤት ስለሚገኝ ወደዚያው ተጓዝን። ቀጥለንም ወደ ቤተልሔም ሂደን ኑሯችንን ጀመርን።
ቤተልሔም የመጋቢ ለማ ሀገር በመሆኑ በአካባቢው ብዙኅ ዘመድ አግኝተናል። በተለይ ፊትአውራሪ በየነ ንጉሤ ፣ ፊትአውራሪ ዘለቀ አንበርብርና ግራአዝማች ወንድአውክ ተድላ የሚባሉ የእናቴ የአክስት ልጆችና ታናሽ ወንድሟን ስላገኘን ኑሯችን የተሳካ እንዲሆን የእነርሱንና የሌላውም ዘመድ ትብብር አልተለየንም። ቤተልሔም እንደደረስን ወንድሞቿ ለእናቴ ታች ጋይንት ከርስት አበል ተሰብስቦ ብዙኅ ዓመት የቈየ ሦስት ጉድጓድ ገብስ ሰጧት። ይህን እኽል ለማቅናት መንገድ ተፈልጐ ከእስቴ የመጡ ብዙኅ አጋሰስ ከያዙ ነጋዴዎች ጋር ተስማምተው ጉድጓዱን ለማስረከብ ከቦታው ተገኝተን ስለነበር ጉድጓዱ ሲከፈት ገብሱ በስብሶ ስለነበር የወጣው ሽታ ከፍተኛ በሽታ የሚያስከትል መስሎን ነበር። እነዚያን የበሰበሱ ሦስት ጉድጓድ ገብስ በጅምላ በ፲፮ ማሪአ ቴሬሳ ብር ሸጠን ታላቅ ገቢ አግኝተን ወደ ቤተልሔም ተጓዝን።