በዚህ ኑሮ ችግር በገጠመን ሰሞን እንግሊዞች በአይሮፕላን ልዩ ልዩ ዕቃ አምጥተው ከአየር ስለጣሉ ዕቃውን አስነሥተው ለማስረከብ ደጅአዝማች ወልደሥላሴ መሸሻ የሚባሉ ዘመዴ በብዙኅ ሠራዊት ታጅበው ሲመጡ ከመንገድ ላይ ስጫወት ስላዩኝ አስጠርተው አነጋገሩኝ። እንደአጋጣሚ የእኝህ ሰው መኖሪያ ቤት በዚህ አካባቢ ስለሆነ እርሳቸውና ሠራዊታቸውም በምግብ አልተቸገሩም ነበር። በዚያን ቀን ሲያዩኝ ረሃብ እንደጐዳኝ ተረድተው ያነጋገሩኝ ነገር “አጐትህ ከእኔ ጋር ስትሄድ ቢያዩህ ደስ ስለማይላቸው ቀድመህ ሂደህ ከዚያ ማዶ ከተራራው አጠገብ ከሚገኘው በር ላይ ብትጠብቀኝ ወስጄ አብረን አድረን በማግሥቱ ወሬው ሳይሰማ እመልስሃለሁ” ስላሉኝ የሆድ ጉዳይ ሆነና ከሚመለሱበት ጊዜ ቀድሜ ከበሯ ላይ ቈሜ ጠበቅኋቸውና አብሬ ሄጄ ታላቅ ድግስ ስከሰክስ አመሸሁ። ከንጋቱ ላይ የተኵስ ድምፅ በብዛት ተሰማ። ምክንያቱም በትክክል ባናውቀውም ጦርነት መነሣቱን በመገመት ደጅአዝማች ወልደሥላሴ መሸሻ ሠራዊታቸውን ይዘው አሠራ በሚባለው ወንዝ በኵል ደባርቅ የሚገኘውን የተከበበውን ጦር ለመውጋት ሲንቀሳቀሱ የእኔ ጓደኛ የሚሆን ወንድ ልጃቸውንና እኔን ከቤት እንዳንወጣ አዘው ሄዱ። ጥቂት ከቈየን በኋላ ልጃቸው ስላደፋፈረኝ እኛም ጕዟችንን ወደዚያው አደረግንና ከወንዙ አጠገብ ስንደርስ ሰልፋቸውን አሳምረው ወደ እኛ ከሚመጡ ባንዳዎች ጋር ፊት ለፊት ተገናኘን። እኛም ደንግጠን ወደ ኋላ ስንሮጥ ወታደሮቹ ልጆች መሆናችንን ተረድተው ይመስለኛል ሳይተኵሱብን በመቅረታቸው ወደ ቤታችን በደኅና ደረስን።
ኋላ እንደተረዳነው ደባርቅ የነበረው የኢጣሊያ ጦር በውድቅት ሌሊት ከሠፈሩ ለቆ በራስ አያሌው ብሩ ሠራዊት ላይ አደጋ ስለጣለ አርበኛውና ራስ አያሌው ብሩም በታላቅ ጀግንነት ሲዋጉ አድረው ቍጥሩ የበዛ ሕዝብ አልቆ በዚሁ ቀን ጦርነት ራስ አያሌው እግራቸው ተሰብሮ ሲማረኩ ፣ ደጅአዝማች መርሶ አያሌውና ደጅአዝማች ሺበሺ ሞተዋል በተረፈ ያለቀው ሕዝብ ቍጥር ሥፍር ስላልነበረው ኋላ የየወገኑን ሬሳ ለሚፈልገው ዘመድ ሁሉ አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። እንዲያውም የደጅአዝማች ሺበሺ አስከሬን የተገኘው ከአንድ ወርኅ በኋላ ነበር። ከላይ እንደገለጽሁት እንጀራ በልቼ አድሬ እንድመለስ በደጅአዝማች ወልደሥላሴ መሸሻ ተጋብዤ ከሠፈሩ በሌለሁበት ቀን ሌሊቱን አደጋው ሲደርስ የሚገርመውና የሚያስደንቀው አብረውኝ የሚያድሩት ወጣቶች አብዛኛው ማለቃቸው ነው። እኔ ግን በዚህ ተአምር ቅልውጥ ሄጄ ተረፍሁ።