ደጅአዝማች ወልደሥላሴ መሸሻ ሙሉውን ቀን ሲዋጉ ውለው ወደማታ አካባቢ ወደ ቤታቸው በተመለሱ ጊዜ የራስ አያሌው ብሩን መማረክና የሕዝቡን እልቂት በይፋ ስለተነገረ እኔ በዚህ ጊዜ ትልቅ ሽብርና ውዥንብር ስለተሰማኝ የማያቋርጥ ልቅሶዬን ተያያዝሁት። ደጅአዝማች ወልደሥላሴም በሁኔታው በጣም ስለተቸገሩ ራስ አያሌውና እርሳቸውም ለእኔ እኵል የአንድ ቅድመአያት ልጆች መሆናችንን ጠቅሰው ይህን ያህል መሸበር እንደማይኖርብኝ ለማፅናናት ከፍተኛ ጥረት አደረጉ። ሰሚ ግን አላገኙም። ሁኔታው በጣም ስላሳሰባቸው ሌላ ዘዴ ፈለጉ። የሰሜንን ጦር የሚመሩት ደጅአዝማች ነጋሽ ወርቅነህ የአያቴ የወንድም ልጅ ስለሆኑ የጦር አለቃውም ፊትአውራሪ በሪሁን አደመ የአባቴ ትልቅ ወንድም ልጅ ስለሆነ ወደ እነርሱ ቢልኩኝ መንፈሴ እንደሚረጋጋ አስበው ይህን እቅድ ነገሩኝ። ምንም እንኳ ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት ዘመዶቼን የማላውቃቸው ቢሆንም ሃሳባቸውን በደስታ ተቀበልሁት። እርሳቸው ወስዶ እንዲያስረክበኝ ከመልእክት ጋር ላኩኝ።
ከደጅአዝማች ነጋሽ ወርቅነህ የጦር ሠፈር ከሰዓት በኋላ ገደማ ስንደርስ የፊትአውራሪ በሪሁን አደመ ጦር ወደ ሠፈሩ ለመሄድ ሲጓዝ ፊት ለፊት ገጠመን። ይዘውኝ የሄዱት የደጅአዝማች ወልደሥላሴ የጦር አዛዥ ከመንገድ ላይ እጅ ሲነሡ ከደጅአዝማች ወልደሥላሴ ተልከው መምጣታቸውን ስለተናገሩ መልእክቱን እንዲናገሩ በቅሎውን ገቶ ሲቆም እርሳቸውም እኔን አስቀድሞ “የአጐትዎን ልጅ ዳኘው ወልደሥላሴ” ብለው ንግ ግራቸውን ሳይጨርሱ ከበቅሎቅ ፈጥኖ ወርዶ አቀፈኝ። ከራስ አያሌው ጋር መኖሬን ስለሚያውቅ ሞቷል ብሎ የገመተ ስለሆነ ተርፌ በመገኘቴ በጣም ተደሰተ። ጦሩ ገና ከደጅአዝማች ነጋሽ ወርቅነህ ሠፈር ሲወጣ በመገናኘታችን የእኔን መምጣት ለእርሳቸው ሳይነግር መሄድ ስላልፈለገ እኔንና ያመጡኝን ሰዎች ይዞ ገባና ደስታውን ነገራቸው። እርሳቸውም በታላቅ ደስታ ተቀብለው ሰዎቹን አመስግነው ከዚያ እንዳድር ጠየቁ። ፊትአውራሪ በሪሁን “የዛሬን ከእኔ ጋር አድሮ እንዲመጣ ይፍቀዱልኝ” ብሎ ጠይቆ ስለፈቀዱለት ጥቂት ካጫወቱን በኋላ ጉዞአችንን ቀጥለን ወደ ፊትአውራሪ በሪሁን ሠፈር ደረስን።
የጦር ሠፈር እያልሁ የምጠራው ሁሉ የሰዎች መንደር ነው እንጂ ጦሩ ሠርቶ የሠፈረበት አይደለም። አሁን የፊትአውራሪ በሪሁን ሠፈር ሆኖ ያገኘሁት እዚያ አካባቢ የታወቁ ሀብታም ሰው ከመሆናቸውም በላይ እኝህ ሰው ቀደም ብለው የፊትአውራሪ በሪሁንና የእኔን አክስት ወይዘሮ አያልነሽ ረታን አግብተው የነበሩ ሰው በመሆናቸው እርሳቸውም በታላቅ ደስታ ተቀብለው የምበላው በፍጥነት እንዲቀርብልኝና ያን የጐፈተውን ጠጕሬን ሊላጭ ሲሰናዱ የጠላት ጦር መጥቶ ከቃፈር ጦር ላይ አደጋ በመጣሉ ተኵስ ስለተሰማ ወዲያው ጥሩንባ ተነፍቶ በፍጥነት ጠላት ወደመጣበት በኵል ጉዞ ሲጀመር እኔም አብሬ ፊትአውራሪ በሪሁንን ተከትዬ መጓዝ ጀመርሁ። ከአንድ ዳገት ላይ ስንደርስ ፊትአውራሪ በሪሁን ወደ ኋላ ሲመለከት የእኔን መምጣት በማየቱ ተቆጥቶ ከመንደሩ ብዙኅ ያልራቅን ስለሆነ ተመልሼ እንድሄድ ሲያዘኝ የለበሰውን ኩታ አውልቆ ሰጠኝና ይዤ እንድሄድ አጥብቆ አዘዘኝ። ትእዛዙን ባልወደውም ጥቂት ከቆየሁ በኋላ የመትረየስ ተኳሾችና አጃቢዎቻቸው ስለመጡ አብሬ እንድሄድ ጋብዘው ወስደው እነዚህ መትረየስ ተኳሾች በአንድ ተራራ ላይ ሆነው መትረየሱን ሲያንኳኩት እጅግ ደስ ይል ነበር። የመትረየሶቹ አጃቢዎችና ጠባቂዎች የጦርነቱ መሟሟቅ ወኔያቸውን ስለገፋፋው ወደፊት ገሥግሠው ከእግረኛው ሠራዊት ጋር በመቀላቀላቸው ከመሸ በኋላ ወደ ሠፈር ለመሄድ ስንነሣ ጓዙን ማለት የጥይቱን ሣጥኖች የሚሸከም በመጥፋቱ የተቸገርን ቢሆንም እኔም ጭምር የሸክሙ ተካፋይ ሆኘ ጉዟችንን ብንጀምርም ዘማቹ ጦር ፊትአውራሪ በሪሁን ጭምር ወደ ሠፈር ገብተው ሲቆጣጠሩ እኔ እንግዳውና መትረየሶቹም ተመልሰው ባለመግባታቸው ትልቅ ሽብር ተፈጠረና ጦሩ እንደገና ወደ ኋላ ተመልሰው ወደ እኛ ሲመጣ ከመንገድ አገኘነውና ታላቅ ደስታ ሆነ። ፊትአውራሪ በሪሁን በመጀመሪያ በተገናኘንበት ቀን እንደዚህ ያለ ችግር በመፈጠሩ መቆጣቱ በግልጽ ቢታይም ምንም አልተናገረኝም። በጦር ግንባር መዋል የተለማመድሁ ቢሆንም በዛሬው ቀን ግን መትረየስ ተኳሾች የአለቃቸው ወንድም መሆኔን በመረዳት ብዙኅ ጥይት እንድተኵስ በማድረጋቸው ተደስቼ ነው የዋልሁት።