Editorial Note:
I will keep making the joke about both September 11th and January 6th being holidays of the Ethiopian Orthodox Tewahdo Church and not to be remembered otherwise, as either days of terrorism or freedom fighting. January 6th is Orthodox Christmas Eve, and today September 10th is of course EOTC New Year’s Eve. Tomorrow is not only New Year’s Day, felicitous 2017 and the Era of St. Matthew to you all, but it is also the 50th anniversary of the Communist Revolution in Ethiopia. The most Godforsaken of all days in our history, in my very humble opinion. To celebrate, here is the first chapter of my maternal grandfather’s memoir. He was an anti-communist who served the communist regime for six months as governor of his home state of Gwender (Gonder), in order to arm his people. He rebuked the next regime of pseudo-linguistic-federalism at its inception. And he is ultimately a proud product of the millenia-old absolute monarchy of Ethiopia, which he served as Ambassador, that repelled the Italians twice (once in his lifetime).
For now, I will keep focusing on: his Amharic memoir, Blanc’s memoir, other primary sources, and scriptural interpretation. A future English translation of his Amharic memoir will Godwilling in due time be made available to you all. Keep me in your holy prayers.
Happy new year! Or inkwan le’riise 3wde 3met aderesachu (thankfully, He brought you all to the head of the cycle of the year).
ውጣ ውረድ የበዝኃበት ሕይወት
ይህ መጽሐፍ አዘውትረው መልካም ሲመኙልኝና ሲያስበሉኝ ለነበሩት አያቴ ለእማሆይ ጥሩነሽ ገብረመድኅንና አባትና እናት ሆነው በጥንቃቄና በሥነሥርዓት ላሳደጉኝ እናቴ ለወይዘሮ እጅጊቱ ተድላ መታሰቢያ ይሁንልኝ።
ዳኘው ወልደሥላሴ ረታ ፲፱፻፹፯ ዓመተ ምሕረት
የአርታዒ አጭር ማሳሰቢያ
የአንድአንድ ልጅና የአንድአንድ ልጅልጅ ቤተሰብእውን የመውደድ ኀላፊነት አለው። ከእነዚህ ብዙኃን ፣ ጥቂቶች የቤተሰብአቸውን ታሪክ ጠባቂና ዘጋቢ የመኾን ተልዕኮ ይኖራቿል። ለእኔ ቤተሰብእ እኔን ከኋለኞቹ ቍጠሩኝ።
ኄኖክ ኤልያስ ነጋሥ
መግቢያ
በኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜው የተለያዩ መንግሥታት ሥልጣን ይዘዋል። ከእነኝህ መንግሥታት ጐን በመሠለፍ ልዩ ልዩ ተግባር ያከናወኑ ግለሰብእ እንደነበሩ ሁሉ ባንፃሩ ደግሞ የተባሉትን መንግሥታት አቋምና ፖሊሲ (policy) በመቃወም ብዝኁ የተሰቃዩና የተገደሉም ነበሩ ፣ አሁንም አሉ ፣ ለወደፊትም ይኖራሉ።
የግለሰብእ ታሪክ የአንድ አገር ታሪክ ሊሆን አይችልም። ሆኖም ግለሰብእ በሕይወት የደረሰባቸው ውጣ ውረድ የተጫወቱት ሚና ያበረከቱት አስትዋጽዖ ወዘተ ተደማምሮ በትክክል ሲቀርብ የአንድን አገር ታሪክ ለመጽሐፍ ለሚፈልጉ ሞያተኞች ምሁራን በምንጭነት በኩል ዓይነተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል። ሕዝብም ከድርጊታቸው ከእምነታቸውና ከስቃያቸው ብቻ ሳይሆን ከሽተታቸውም ብዝኁ ነገር ለመምሃር ይቻላል።
አቶ ዳኘው ወልደሥላሴ ቀደም ሲል የእስራት ዘመን በአበሻ አገር እንዲሁም የአድዋ ዘመቻና የአፄ ምኒልክ አነሣስ የተሰኙትን ሁለት በውጭ አገር ቋንቋ የተጸሐፈ መጽሐፍት ወደ ዐምሐርኛ ተርጕመው ለአንባቢያን ማቅረባቸው የሚታወስ ነው። ይህም ድርጊት ልምርምር ለጥናትና ለታሪክ ያላቸውን ዝንባሌ ይጠቁማል።
አሁን ደግሞ ውጣ ውረድ የበዝኀበት ሕይወት በሚል ርዕስ የግል የሕይወት ታሪካቸውን ጽሕፈዋል። የአስተዳደግ አከባቢያቸው ምን ይመስል እንደነበር የኢጣልያ ፋሽስት (fascist) ወታደር ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የደረሰባቸው ችግር ዘመናዊ ትምህርት እንዴት ለመቀሠም እንደቻሉና ከጐንደር ወደ አዲስ አበባ ሄደው በወቅቱ የመምህራን ማሠልጠኛ ኰለጅ ይባል በነበረው ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ተመርቀው በልዩ ልዩ ዘርፎች የትምህርት ሚኒስቴር (minister) ተዛውረው ፣ በግብፅ ፣ በቫቲካን ፣ በከሰላ ፣ በሳውዲ አረቢያና በመጨረሻም በአምባሳደርነት ማዕረግ በሰሜን የመን ኋላም የጐንደር ክፍለሀገር ዋና አስተዳዳሪ ሆነው እንዴት እንደተሾሙና ሽአለቃ መልአኩ ተፈራ የሚባለው የደርግ አባል አፍኖ ወስዶ ሊረሽናቸው ሲል እንዴት እንደተረፉ አብራርተው ጽሕፈዋል።
ውጣ ውረድ የበዝኀበት ሕይወት በአጽሐጽሐፉ ፣ በአቀራረቡ ፣ በቋንቋ ጥራቱና በታሪክነቱ ተነባቢ ሲሆን ፤ ሌሎችንም ኢትዮጵያውያን የግል ሕይወት ታሪካቸውን ጽሕፈው ለአንባቢያን እንዲያበረክቱ የምያደፋፈር ነው።
ቀኝአዝማች ሣህሌ አዩ
ዳኘው ወልደሥላሴ ረታ እባላለሁ። የተወለድሁት ታኅሣሥ ፳ ቀን ፲፱፻፳ ዓ፡ም በጐንደር ክፍለ ሀገር ወገራ አውራጃ ልዩ ስሙ ዳባት ገብርኤል ከሚባለው ክልል ውስጥ ነው።
የትውልድ ሐረግና እድገት ፡ ከ፲፱፻፳ እስከ ፲፱፻፴፯ ዓ፡ም
ወላጆቼ ቀኝአዝማች ወልደሥላሴ ረታና ወይዘሮ እጅጊቱ ተድላ መኰንን ይባላሉ። ቀኝአዝማች ወልደሥላሴ በአባታቸው ወልቃይት ጠገዴ ፣ ቆላ ወገራ ሲሆኑ ፣ በእናታቸው የሰሜን ተወላጅ ናቸው። የእናታቸው እናት ሀገር ደግሞ ጐጃም ነው። የእናቴ ትውልድ ጐንደር ክፍለ ሀገር ጋይንት ሲሆን አንዱ አያታቸው ደብረታቦር አውራጃ አሞራ ገደል ከሚባለው አካባቢ ተወላጅ ናቸው።
እነዚህ ከሰሜንና ከደቡብ ጐንደር የሚወለዱ ወላጆቼ እኔንና ትንሽ ወንድሜን ደምሴ ወልደሥላሴ ወለዱ።
የወላጆቼን ትውልድ ሐረግ ዘርዘር አድርጌ ለመመዝገብ እወዳለሁ። የአባቴ የቀኝአዝማች ወልደሥላሴ አባት ፊትአውራሪ ረታ ሲሆኑ ፣ እርሳቸውም የጠገዴው ተወላጅ የደጅአዝማች ክንፉ ልጅ ናቸው። እናታቸው ወይዘሮ ኂሩት ጥሶ የቆላ ወገራ ተወላጅ የደጅአዝማች ጥሶ ጐበዜ ትንሽ እኅት ናቸው። ከዚህ ጋብቻ ብዙኅ ልጆች የተወለዱ ሲሆን ማለት አያቴ ፊትአውራሪ ረታ ክንፉ የበኵር ልጅ ናቸው።
የአባቴ እናት ወይዘሮ ጥሩነሽ ገብረመድኅን የሰሜኑ የራስ ገብረመድኅን ኃይለማርያም ልጅ ሲሆኑ ፣ ራስ ገብረመድኅን ኃይለማርያም የወንድሞቻቸውና የኅቶቻቸው ቍጥር ብዙኅ ቢሆንም ለአባታቸው ለደጅአዝማች ኃይለማርያም ገብሬ የበኵር ልጅ ደጅአዝማች ውቤ ኃይለማርያም ሲሆኑ ፣ ኋላም የወረሼኽ ተወላጅ የሆኑትን ወይዘሮ ኂሩት ጉግሣን አግብተው ደጅአዝማች መርሶ ኃይለማርያምን ደጅአዝማች ብጡል ኃይለማርያምንና ወይዘሮ የውብዳር ኃይለማርያምን ወልዷል። ራስ ገብረመድኅን ኃይለማርያም ከሁሉም በእድሜ የሚያንሱ ከመሆናቸውም በላይ በእናታቸው የወገራ ተወላጅ የደጅአዝማች አምሳሌ የልጅ ልጅ በመሆናቸው በሰሜንና በወገራ ሰፊ የዘር ሐረግ አላቸው።
ራስ ገብረመድኅን ኃይለማርያም ከወንድሞቻቸውና ከእኅቶቻቸው ለየት የሚያደርጋቸው ቍጥር ፵፭ ይደርሳል የሚባል ልጆች መውለዳቸው የዘሩን ቍጥር እጅግ በጣም ከፍ ያደርገዋል። እንግዲህ የአያቴን የወይዘሮ ጥሩነሽ ገብረመድኅን እናት ከጐጃም አምጥተው አያቴን ፊትአውራሪ ረታ ክንፉን አግብተው ወልደሥላሴ ፣ አያልነሽ ፣ ዘውዱና ፣ ዘነበች የሚባሉ አራት ልጆች ወልደዋል። የእኔ አባት ቀኝአዝማች ወልደሥላሴ ረታ እኔ የሁለት ዓመት ልጅ ሳለሁ ትንሽ ወንድሜ የአንድ ዓመት ልጅ ሳለ ሲሞቱ። ሌላው ልጅ ዘውዱ ረታ የተባለው አጐቴም በወጣትነቱ ወርኆች ስለሞተ ሴት አያቴ ከባድ ኀዘን ስለገጠማቸው በአርባ ዓመታቸው መነኰሱ። ተከታትሎም የኢጣሊያ ጦርነት መጥቶ ሀገራቸው ከመከራ ውስጥ በመግባቷ ኀዘናቸው እጅግ እየመረረ በመሄዱ ሥጋዊውን ዓለም መንነው ወደ ዋልድባ ስቋር ገዳም ገቡ።
እናቴ ወይዘሮ እጅጊቱ ተድላ መኰንን በጐንደር ክፍለ ሀገር ጋይንትና ደብረታቦር አውራጃዎች እንደሚወለዱ ጠቅሻለሁ። አባታቸው ቀኝአዝማች ተድላ መኰንን ትውልዳቸው ሙጃን ፣ ሰማዳንና ፣ በሽሎን ተሻግሮ ኮሬብን ያካትታል። ቀኝአዝማች ተድላ መኰንን በትውልዳቸው የገበሬ ቤተሰብእ ናቸው። አያታቸው ሀብቱ ገብረመድኅን በእርሻ የከበሩና የታወቁ ሰው በመሆናቸውም በላይ አርባ የሚሆኑ ልጆች የወለዱ በመሆናቸው በሀገሬው አነጋገር ዘራቸው ወሎንና ሙጃን ፣ ሰማዳን ያጥለቀለቀ በመሆኑ የሀብቱ ገብረመድኅን ዘር ድንጋይ ቢፈነቀል ይገኛል እየተባለ ስለሚነገር ከዚህ ዘር የሚወለድ ሁሉ ተጐንብሶ ውኀ ቢጠጣ አይሠጋም ይባልለታል። የእኝህ ሰው የልጅ ልጅ ተድላ መኰንን በልጅነታቸው ከእረኝነት ጠፍተው ወደ አዲስ አበባ መጥተው ለእተጌ ጣይቱ ከሥልጣን ላይ ሥልጣን እየጨመሩ ከከፍተኛ ቦታ አድርሰዋቸዋል። ቀኝአዝማች ተድላ መኰንን በዚህ አጋጣሚ ብዙኅ ሰዎችን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር ይባላል።
ሴቷ አያቴ ወይዘሮ ዘገየች ለማ ሲባሉ ትውልዳቸው በእናታቸው ጋይንት የፊትአውራሪ መረዋ የልጅ ልጅ የደጅአዝማች ብርሌ መኰንን የአክስት ልጅ ያደጉት በደጅአዝማች ብርሌ ቤት ነው። አባታቸው መጋቢ ለማ የሚባሉ የቤተልሔም መጋቢ ልጅ ናቸው። ደጅአዝማች ብርሌ ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው ሲመጡ ዘገየች ለማ አብረው ስለመጡ አዲስ አበባ ከቀኝአዝማች ተድላ መኰንን ጋር በመጋባታቸው አንዲት ሴትና አንድ ወንድ ልጅ ወልደው ቀኝአዝማች ተድላ በድንገተኛ ሕመም ታመው ስለሞቱ ወይዘሮ ዘገየች ለማ ሁለት ልጆቻቸውንና ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን ይዘው ወደ ሀገራቸው ጋይንት ሲሄዱ በየቦታው የነበረውን ርስትና አዲስ አበባ የነበራቸውን ሰፊ የከተማ ቦታ ጥለውት በመሄዳቸውና ሳይመለሱበት በመቅረታቸው ከኢጣሊያ ጦርነት በፊት በጠፍ መሬትነት ተከፋፍሏል። ወይዘሮ ዘገየች ለማ በጋይንት ፣ በሰዴ ፣ በቤተልሔም ሰፊ ርስት ስለነበራቸው ፣ የሸዋውን ርስት ዋጋ የሰጡት አይመስልም።
እንግዲህ ከላይ እንደገለጽሁት በጐንደር ክፍለ ሀገር ከገበሬው ፣ ከወታደሩ ፣ ከካህኑ ፣ ከመኳንንቱ ፣ ከመሳፍንቱና ፣ ከነገሥቱ ዘር ከሚቈጥሩ ቤተሰብእ ከመወለዴም በላይ አምስት ቅድመአያቶቼ እያንዳንዳቸው ቍጥራቸው አርባና ከአርባ በላይ ልጆች በመውለዳቸው የጐንደርም ሕዝብ የዘር ቈጣሪነት ባሕርይ ያለው ቢሆንም የጢሰኝነትና የገባርነት ታሪክ የሌለው ፣ ዘመድ ከዘመዱ የሚጣላበት ምክንያት ባለመኖሩ የዘሩን ግንድ የማወቅ ግዴታ ያለው ሕዝብ ስለሆነ ተደጋጋፊና ተቀራራቢ ሕዝብ የሚገኝበት ሀገር በመሆኑ ደጅአዝማች ከገበሬው በትውልድ ሐረጉ ልዩነት ስለማይኖረው እኵልነት የሰፈነበት ሕዝብ የሚገኝበት ሀገር ነው።
አባትና እናቴ ከመጋባታቸው በፊት ሁለቱም ጋብቻ መሥርተው ስለንበረ ፣ አባቴ አስታጥቄና ሙሉ የሚባሉ ሁለት ልጆች ሲኖራቸው እናቴ ደግሞ አልጋነሽ ፣ አሰለፈች ፣ አየለና ፣ መነን የሚባሉ አራት ልጆች ነበሯቸው። ከሁለቱ ጋብቻ የተገኘነው እኔና ደምሴ የሚባል ወንድሜ ብቻ ነበርን።
ከላይ እንደገለጽሁት አባቴ ገና ሁለት ዓመት ልጅ ሳለሁ ጠንቅቄ ሳላውቃቸው በሞት ስለተለዩኝ ያለ አባት ማደጉን ጀመርሁት። በዚያን ጊዜ በነበረው ሥርዓት መሠረት አባቴ እንደሞቱ እርሳቸው ሳሉ ይተዳደሩበት የነበረውን ሀገር እኔ በእናቴ ሞግዚትነት እንዳስተዳድር መሾሜን ካደሁ በኋላ መረዳት ቻልሁ። አስተዳደጌ እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ ትልቅ ሰው ነበር። እንክብካቤ የሚሰጡኝ ብዙኅ ዘመዶቼና የአባቴ ሰዎች ነበሩ። ትንሽ ከፍ እያልሁ ስሄድ ማንኛውም ነገር እንዳውቅና አንዳንድ ጊዜም ያላልሁትንና ያላደረግሁትን እያወሩ ያሞጋግሱኝ ነበር።
አስተዳድረው የነበረው ሀገር አጅሬ የሚባል ሲሆን በቆላ ወገራ ውስጥ የሚገኝ ሥፍራ በመሆኑ ከሞላ ጐደል ዘመድ የሚበዝኀበትና ድጋፍ የማገኝበት ሀገር ስለሆነ ሁሉም ነገር በግድና በኃይል የሚፈፀም ነገር አልነበረም። ይህ አፈፃፀም ከጥንት ከአያቶቼ ተያይዞ የመጣ አሠራር ስለነበረ በእኔም ጊዜ ሁኔታው አልተለወጠም። ከእናቴ ጋር ሆነን ብዙኅ ጊዜ የምናሳልፈው ዳባት ከሚባል የደጅአዝማች አያሌው ብሩ ከተማ ስለነበረ ደጅአዝማች አያሌው ልዩ እንክብካቤ ያደርጉልን ስለነበር በአባታችን ሞት ምክንያት የጐደለ ነገር አልነበረም።
በ፲፱፻፳፯ ዓ፡ም የኢጣሊያ ጦርነት ወሬ ይነፍስ ስለነበረ በሀገሩ ባሕል መሰረት በማስተዳድረው ሀገር የሚገኘውን ተዋጊ ጦር ይዤ መዝመት እንዳለብኝ ይወራ ስለነበረ የመጣውን ጣጣ ሳላውቀው የጦር አዝማች ሆኜ የምዘምት በመሆኔ ብቻ ፈንድቄ ነበር። ስለሆነም ፤ ሁልጊዜ ከሚያስቡልን ከትልቁ ሰው ከደጅአዝማች አያሌው ብሩ እንዳልዘምት ትዕዛዝ ስለደረሰ ደስታዬን ቀጩት። የቆላ ወገራን ጦር በሙሉ ግራአዝማች ሊላይ ደሴ ፣ ኋላ ደጅአዝማች ፣ ይዘው እንዲዘምቱ ተደረገ።
ታሪክ እንደሚያስረዳን ጣሊያን የዓድዋን ድል ለመበቀል በከፍተኛ ደረጃ ተዘጋጅታ የመጣች ስለሆነ ምንም እንኳ ሕዝቡ ሽረ ላይ ከፈተኛ መተላለቅ ቢያደርግም የመርዙን ቃጠሎና መከራ ሊቋቋመው አልቻለም። ብዙኅ ሠራዊት አልቆና ቈስሎ የተረፈው በተጐሳቀለ ሁኔታ ሲመለስ ልቅሶና ጩኸቱ በየመንደሩ ይሰማ ጀመር። በመንደር ውስጥ የቈየነውም ጭንቀቱና ፍርሃቱ እጅግ አሳሰበን። በተለይ እናቴ ከባድ ጭንቅ ውስጥ ገቡ። የሚሆኑትን አጡ።
በካፕቴን የሚመራ የድል አድራጊው ጦር አጅሬ ከእኛው ባድማ ላይ መጥቶ ሠፈረና ሕዝቡ መሣሪያውን እንዲያስረክብና የሰላም ኑሮውን እንዲቀጥል አወጀ። ሕዝቡ ግን ፈፅሞ መንፈሱ ድል ያልተመታ ስለሆነ ለጦርነት በመዘጋጀት ላይ እንደነበረ መረዳት ይቻላል። ጣሊያኑ ወደ እኛይቱ መሬት ሲመጣ አስቀድሞ የሰውን ታሪክና ይዞታ በሚገባ አጥንቶ የመጣ ስለሆነ አጅሬ በሠፈረ በሳምንት ጊዜ ውስጥ እኔንና ወንድሜን ወደ ኢጣሊያው ሠፈር እንድንቀርብ በመታዘዙ እናታችንና ዘመድ ወዳጅ ሁሉ በከፍተኛ ፍርሃትና ሽብር ላይ ወደቁ። ውባዬ ለገሠ የሚያደርጉትን የሚያውቁ ብርቱ ሽማግሌ ስለነበሩ በድፍረት ይዘውን ሄዱና ተገናኘን ፈረንጁም በክብር ተቀበለን። እኛም በክብርና በምቾት ያደግን ልጆች ስለነበርን ክብራችን የተጠበቀልን ልጆች ሆነን እንዳገኘን ገመተን። ወዲያውኑ ውሎ ሳያድር የድሮ ግዛቴን ሰጥቶ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ስብከቱን ቀጠለ እኛም በደኅና ወደቤታችን በመመለሳችን ታላቅ ደስታ ሆነ።
የሀገሬው ጀግና ፣ ይህን አህያ እናሳየዋልን ፣ የሚለውን አነጋገር በመብዝኀቱ ወሬው ከኢጣሊያው ጆሮ ሳይደርስ አልቀረም። ብዙኅ ጊዜ ውባዬ ለገሠ ሳያወላውሉ ወዲያውኑ ወደ ቆላ ወገራ በረሃ ይዘውን ሸሹ። ይህ በሆነ በጥቂት ቀናት ውስጥ አርበኛው ተነሣሥቶ የኢጣሊያኑን ሠፈር ለመደብደብ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን በይፋ ይሰማ ስለነበረ ጣሊያኑ በወሬው ተሸብሮ የሰበሰበውም የጦር መሣሪያ አቃጥሎ ሸሽቶ አመለጠ። አርበኛው ግን የተቃጠለውን መሣሪያ የዋንዛ እንጨት እየጠረቡ መልሰው በመገጣጠም ጦርነቱን በይፋ ተያያዙት። እኛም ውባዬ ለገሠ ቀደም ብለው አሸሽተውን ወደ ነበረው መንደራችን ተመልሰን መኖር ጀመርን። ከላይ እንደገለጽሁት ያለንበት ሀገር ዘመድ በብዝኀት የሚገኝበት በመሆኑ ሕዝቡ ለመኖር የሚያስችለንን ነገር በሚገባ እየሰጠ ኑሯችን ሳይበላሽ መኖሩን ቀጥለናል።
አጅሬ ሠፍሮ የነበረው የኢጣሊያው ጦር ሸሽቶ ካመለጠ በኋላ መሬቱም ተራራማ አባጣ ጐባጣ የበዝኀበት በመሆኑ የጠላት ጦር ደፍሮ ለመምጣት ጊዜ ውስዶበታል። ሰፊ ዝግጅት ካደረገ በኋላ ጃኖራን ፣ ቆላ ወገራን ፣ ጠገዴንና በአካባቢው ያሉትን የቆላ ሀገሮች ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ አቅደው ቍጥሩ ከ፲፪ ሺህ በላይ የሚሆን ወታደር ከፍተኛ ዝግጅትና ትጥቅ አስይዘው አንድ ቀን በምሽት ጕዟቸው ወደ ቆላው አደረገ። አርበኛው ወደ ደጋው ጣልያኑ ወደሚገኝበት እየተጓዘ ጥቃት ያደርስ ስለነበረ ፤ የኢጣሊያው ጦር ወደ ቆላው በተጓዘበት ቀን ገብረማርያም ደስታ ፣ በኋላ ፊትአውራሪ ፣ ከሚባል ሰው ቤት ላይ አደጋ ጣለ። ይህ አርበኛ አሥራ ሁለት የጠላት ጦር ገድሎ ሲያመልጥ ጦርነቱ ተጀመረ። ቀንጣ ከሚባለው ሀገር አካባቢ የጠሊማይን ወንዝ ከመያዙ በፊት የጠላት ጦር ባለበት ቦታ ስለተገታ የተኵስ ድምፅ በየአካባቢው ያለውን ሕዝብ ስለቀሰቀሰው ፣ ከርሑቅ ቦታ ያለውም አርበኛ ወሬውን እየሰምዐ ተሰባስቦ የተጧጧፈ ጦርነት ተጀመረ። የጠላት ጦር ውኃ በሌለበት አካባቢ ግጭት በመጀመሩ ትልቅ ችግር ፈጠረባቸው። የውኃው ጥም እያሳበዳቸው ብዙኅ ወታደሮች ዓይናቸውን ጨፍነው በጠላት እጅ ወደተያዘው ወንዝ እየበረሩ በሚመጡበት ጊዜ ለአርበኛው ጥይት ጥሩ ዒላማ ሆነው አለቁ። በዚህ ሁኔታ ፲፪ ቀንና ሌሊት የወሰደ አስከፊ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ ጥቂት የኢጣሊያ ወታደሮች አምልጠው ከመሄዳቸው በስተቀር የተረፈው ከዚያው ተረፍርፎ ቀረ። አርበኛው በዚህ ጦርነት አስደናቂ ድል ከመጐናፀፉ በላይ ቍጥር ሥፍር የሌለው መሣሪያ ለመማረክ በመቻሉ ለሚቀጥለው ውጊያ ሊያሰናዳው ችሏል።
ይህ ጦርነት የተካሄደው እኔና ቤተሰብኤ ከምንኖርበት ቦታ አካባቢ ቅርብ ስለነበር እኛም ከጭንቅ ላይ ወድቀን ሰንብተናል። ሁሉም ሕዝብ በእግዚኦታና በጸሎት ተይዞ ቆይቷል። ከድል በኋላ የወገን ቍስለኛ ወደ ሠፈር ሲመለስ የሞቱት ደግሞ መርዶው ለየቤተሰብአቸው ይደርስ ጀመርና በየመንደሩ ልቅሶው ይሰምዐ ጀመር። እንደማስታውሰው ከዚህ ጦርነት በኋላ የጠላት ጦር ወደ ቆላው ፊቱን ባያዞርም ጀግናው አርበኛ ግን በየምሽጉ እየዘለቀ ይጨፍጭፍ ነበር።
የሀገሬው ሕዝብ ሁሉም ፊቱን ወደ ጦርነቱ ስላዞረ አርበኛውን ለማበረታታት አለቃውን መርጦ የደጅአዝማችነት ማዕረግ ይሰጠውና ተሿሚውም በበኵሉ ሰዎች እየመረጠ ፊትአውራሪ ፣ ቀኝአዝማች ፣ ግራአዝማች ፣ ባዕለአምባራስ እያለ የሹመት ስም እየሰጠ አርበኛው ሁሉ በሹመት በመጥለቅለቁ ፣ የእርሻው ጉዳይ ተዘነጋና መሬት ጦም አዳሪ መሆኗ ሲገርም ጥቂት ሰዎች ያረሱትን አዝመራም አንበጣ ሙጥጥ አድርጐ ስለበላው አርበኛው የሚገኝበት ቆላው ሀገር ከከፍተኛ ረሐብ ላይ ወደቀ። ከላይ በኵል ደጋው ጠላት የሠፈረበት ሲሆን እኛም ያለንበት ሀገር ከእኽል የተራቈተ ስለሆነ መድረሻ ጠፋ። እኛም የዚሁ የአካባቢውን ችግር ተካፋይ በመሆናችን በሕፃንነት ወርኆች ረሐቡንና መከራውን አብረን ተካፈልን። ሕዝቡ ይህ ሁሉ ችግር ገጥሞት ሳለ ለእኛ ማሰቡን ሳያቋርጥ ካለው ዘርም ብትሆን ያካፍሉን ስለነበር ሙቅ ሾርባ እንኳ ከመጠጣት አላቋረጥንም ነበር። ውሎ አድሮ ከማለቅ የሚያድኅነን ነገር ባለመኖሩ የኢጣሊያንን መንግሥት ምሕረት ጠይቀን ወደ ደጋው እንድንመጣና ከዚያም ወደ እናቴ ሀገር ጋይንት እንድንሄድ ተወሰነ። ይህንም እቅድ ከግቡ ለማድረስ የተከተለነው ዘዴ ፊትአውራሪ ደርሶ ኪዳኑ ፣ ኋላ ደጅአዝማች ፣ የሚባሉ ሰው ሽሬ በተደረገው ጦርነት ቈስለው እግራቸው ተሰብሮ ስለነበር ዳባት ላይ የጠላት ጦር ስላገኛቸው ታክመው ሲሻላቸው ለኢጣሊያ ተቀጥረው ከፈረንጁ በታች ትልቅ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ስለነበር ፤ እኝህም ሰው ወይዘሮ ማሚቴ ዘለለው የሚባሉ የእናቴ የአክስታቸው የልጅልጅ በአባቴ በኵል የደጅአዝማች መርሶ ኃይለማርያም የልጅልጅ ቅርብ ዘማዳችንን ያገቡ ስለሆነ በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም ከኢጣልያኑ ምሕረት እንዲያሰጡን መላላክ ተጀምሮ ነበር። የኢጣሊያው ገዢ ቂም የያዘብን የመስለኛል። ፈጥኖ ምሕረት ባይሰጠንም ውሎ አድሮ ስለፈቀደልን እናቴን ፣ እኔንና ወንድሜን ከነበርንበት ቦታ ሸኝተው ድራድራ ከሚባለው ገደል ሥር ዳባት አቅራቢያ አደረሱን።
በዚህ ቦታ በእንግድነት የተቀበሉን ሰዎች ውዲያው ወደ ቤት እንደገባን ለእኔና ለወንድሜ በእርጐ የተፈተፈተ እንጀራ ሰጥተውን ስንበላ ለእናቴ ግን ለጊዜው ምንም ያላቀረቡላቸው ስለሆነ አዘንሁ። ቢሆንም ወዲያው ብዙኅ ሳይቆዩ እራት አቅርበው ከብዙኅ ጊዜ በፊት ያየነውን እንጀራ ተመገቡ። ያደርንባቸው ሰዎች በአርበኛው ክልል ናቸው ተብለው ቢቈጠሩም ወደ ኢጣሊያው ገበያ የሚሄዱ ስለሆነ በማግሥቱ ረድተው ተራራውን ወጥተን ዳባት ከተማ ደርሰን ከፊትአውራሪ ደርሶ ቤት ገባን።
የገባንበት ቤት ምግብ እንደልብ የሚበላበት ስለሆነ እስክንጠግብ በልተን በሰላም ተኝተን አደርን። በማግሥቱ ጧት ፊታ ደርሶ እኔንና ትንሽ ወንድሜን ወደ ፈረንጁ ወስደው መምጣታችንን ገለጹና ብዙኅ ተነጋገሩ። ምን እንደተነጋገሩ የምናውቀው ነገር አልነበረም። ጣሊያኑ በጣም ክፉ ዓይኑ እንደተመለከተን መረዳት ችለናል። በእኛ በኵል የቀረበው ጥያቄ ይለፍ ተሰጥቶን ወደ ጋይንት ለመሄድ እንድንችል ሲሆን ፣ ከላይ እንደገለጽሁት ከብዙኅ ንግ ግር በኋላ የተሰጠው ውሳኔ ግን ለአሥራ ኀምስት ቀን የዳባትን ዙሪያ መሬት ለእርሻ የተመቻቸ ለማድረግ በላዩ ላይ የሚገኘውን ድንጋይ የሚለቅም በብዙኅ ሺህ የሚቈጠር ሠራተኛ ተሠማርቶ ይለቅም ስለነበር ፣ እኔና ትንሽ ወንድሜ ወደዚህ ቦታ እየሄድን እንድንሸቅል ተወስኖ ተነገረን። ፊትአውራሪ ደርሶ በሁኔታው ያዘኑ ቢመስልም ከዚህ የተሻለ መፍትሔ የሚገኝ አልመሰለኝም። በመሠረቱ ሥራ ሠርተን የማናውቅ ከዚህ በላይ በደረሰብን ረሐብ ሰውነታችን በጣም የተጐዳ ስለነበረ የተመለከተን ሰው ሁሉ ያዝንልን ነበር። ቢሆንም በማግሥቱ ጧት ወደ ምንሸቅልበት ቦታ ሰዎች ወስደው አስረከቡን። ሁኔታው ለእኛ ምንም የሰጠን ስሜት አልነበረም። ይልቁንም ለሸቀል የተሰማራንበት ድንጋይ የመልቀሙ ሥራ እንደኳስ ጨዋታ የቈጠርነው ከመሆኑም በላይ በየቀኑ ዓይተነው የማናውቀውን ትልልቅ ዳቦ ይሰጡን ስለነበረ የተራበውን ሰውነታችን በፍጥነት ያድብረው ጀመር። ማታ ወደ ቤታችን ስንሄድ ተዘጋጅቶ የሚቈየንን ያማረ ምግብ መብላት ያቅተን ጀመር። እናታችንም ሁኔታውን በትክክል ባለመረዳት ከልባቸው ያዝኑና ይጨነቁ ነበር።
ወደ ሮሜ እንድንሄድ የጋበዘንን ልጆች የኢጣልያው ገዢ አዋርዶ በተሾምንበትና በተሸለምንበት በተዝናናንበት የዳባት ከተማ በሸቀላይነት አሥራ ኀምስት ቀን ከቈየን በኋላ ወደ ጋይንት እንድናልፍ ፈቃድ ተሰጠን። ፈቃዱን ባገኘን ማግሥት በጦርና በታንክ እየታጀበ በሚጓዘው በአንዱ ትሬንታ ኳትሮ ላይ ተጭነን ጕዟችንን ወደ ጐንደር ቀጠልን። ቀኑን ስንጓዝ ውለን ጐንደር የደረስነው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ስለነበረ ከተማይቱ በኤሌክትሪክ ብርሃን በቋያ እሳት የምትቃጠል መስላ ስንመለከታት ትልቅ ፍርሃትና ሽብር ተሰማን። ዘመድ ፈልገን ለማግኘትም ከሚኪናው ወርደን በእግራችን ጕዞ ጀመርን። ወደ ፒያሳው አካባቢ ስንደርስ አንድያውን ከተቃጠለ መሬት ላይ የቆምን መሰለን። ከብዙኅ ፍርሃትና ጭንቀት በኋላ ወደ አራዳው አካባቢ የምንፈልገውን አድራሻ አግኝተን ሠፈርን። ጐንደር ብዙኅ ሳንቆይ በትሬንታ ኳትሮ ተሳፍረን ደብረ ታቦር ደረስን። ከዚያም ደጅአዝማች አድማሱ ብሩ ግቢ ገብተን አደርን። የእናታችንን ዘመዶች በብዝኀት ማግኘት ስለጀመርን ችግራችንና ፍርሃታችንም እየቀነሰ መጣ። ደብረ ታቦር በየቦታው እየተጋበዝን የነበርንበትን የረሐብ ሀገር የረሳነው መሰለን። ከዚህም ብዙኅ ሳንቆይ ጕዟችንን ቀጥለን ነፋስ መውጫ ደረስን። በዚህ ከተማ ትንሽ ካረፍን በኋላ ወጣ ብሎ የደሮ ከሚባለው መንደር የእናቴ ወንድም የግራአዝማች ወንድአውክ ተድላ ቤት ስለሚገኝ ወደዚያው ተጓዝን። ቀጥለንም ወደ ቤተልሔም ሂደን ኑሯችንን ጀመርን።
ቤተልሔም የመጋቢ ለማ ሀገር በመሆኑ በአካባቢው ብዙኅ ዘመድ አግኝተናል። በተለይ ፊትአውራሪ በየነ ንጉሤ ፣ ፊትአውራሪ ዘለቀ አንበርብርና ግራአዝማች ወንድአውክ ተድላ የሚባሉ የእናቴ የአክስት ልጆችና ታናሽ ወንድሟን ስላገኘን ኑሯችን የተሳካ እንዲሆን የእነርሱንና የሌላውም ዘመድ ትብብር አልተለየንም። ቤተልሔም እንደደረስን ወንድሞቿ ለእናቴ ታች ጋይንት ከርስት አበል ተሰብስቦ ብዙኅ ዓመት የቈየ ሦስት ጉድጓድ ገብስ ሰጧት። ይህን እኽል ለማቅናት መንገድ ተፈልጐ ከእስቴ የመጡ ብዙኅ አጋሰስ ከያዙ ነጋዴዎች ጋር ተስማምተው ጉድጓዱን ለማስረከብ ከቦታው ተገኝተን ስለነበር ጉድጓዱ ሲከፈት ገብሱ በስብሶ ስለነበር የወጣው ሽታ ከፍተኛ በሽታ የሚያስከትል መስሎን ነበር። እነዚያን የበሰበሱ ሦስት ጉድጓድ ገብስ በጅምላ በ፲፮ ማሪአ ቴሬሳ ብር ሸጠን ታላቅ ገቢ አግኝተን ወደ ቤተልሔም ተጓዝን።
በዚያን ጊዜ የጋይንት መሬት ሲሶና እሩብ ለባለመሬቱ ይመክፈል ባሕል ስለነበረ ብዙኅ መሬት ለእናቴ ስለተሰጠ እኛም ማስጠመኑን በሰፊው ተያያዝነው። በተለይም ጨፋ ወንዝ ማዶ ከሰዴው ክልል ውስጥ የሚገኝ ጥፍያ ተብሎ የሚጠራ ታላቅ ምርት የሚገኝበት ሰፊ መሬት ለእናቴ ስለተሰጠ ጥፍያን ለማረስ ደጅ የሚጠናው ሙክት ስቦ ይመጣ ነበር። ጥፍያ የሚገኘው ምርት ብቻ ለቤተሰብኡ ቀለብና ኑሮውን በጠቅላላ የሚሸፍን ይመስለኛል። ኋላ እንደሰማሁት አንድ ሰው ተጠምኖ ለማረስ ከገባ በኋላ ሳይታወቅ አንዷን የአያቴን እኅት የልጅልጅ አግብቶ ከወለደ በኋላ ይገባኛል በማለት ቀማቸው ማለትን ሰማሁ። በጊዜው ጥፍያ ሳናርስ መኖርን አስለምዶን ነበር።
ምንም እንኳን ኑሮው የተመቸንና የተስማማን ቢሆንም እናታችን ስለዘለቄታው ዕድላችን ስለሚያስቡ ወደ አባታችን ሀገር መልሰው ሊወስዱን ያስቡ ስለነበር በአጋጣሚ ደግሞ ኢጣሊያ ደጅአዝማች አያሌውን ከግዞት አምጥቶ ራስ ብሎ የድሮ ግዛታቸውን እንደሰጣቸው ሲሰማ ሳንውል ሳናድር ጉዟችንን ወደ ጐንደር አድርገን እንደአባት ወደምንቈጥራቸው ሰው ቤት ሄድን። እርሳቸውም በደስታ ተቀብለውን እኔ አብሬ ወደ ዳባት እንድሄድ ሲያደርጉ እናቴና ትንሽ ወንድሜ ግን ከዚያው ጐንደር እንዲቀመጡ ቤትና ቀለብ ሰጥተዋቸው ሄዱ።
ራስ አያሌው ብሩ ወደ ዳባት በተጓዙበት ቀን ቍጥሩ አሥር ሺህ የሚሆን የጦር መሣሪያና ስፍር ቍጥር ከሌለው ጥይት ጋር ስኳር ዶቄቱ በጠቅላላው ልዩ ልዩ ስንቅ በግምት ፪፻ በሚሆን መኪና ተጭኖ ሲሰለፍ ከጐንደር ዋላጅን ተሻግሮ ይታይ ነበር። የኢጣሊያ እቅድ ሀገሩ የጥንት አስተዳዳሪውን ሲያገኝ ሰጥ ለበጥ ብሎ ይገዛል ብሎ የገመተ ሲሆን ራስ አያሌው ብሩ ግን ለይስሙላ የሚደርግላቸውን ሹመትና ሽልማት በደስታ የተቀበሉት ቢመስልም ልባቸው ሸፍቶ ስለነበር ከማስታውሰው ነገሮች መካከል መሣሪያውን ለሕዝቡ ሲሰጡት «ሥራበት» የሚል ትእዛዝ እንደነበረ በትክክል አስታውሳለሁ። በዚህ ሁኔታ መሣሪያውን አድለው ከጨረሱ በኋላ ራሳቸው ለመሸፈት እቅድ ነበራቸው ማለት ነው። እርሳቸውን ለመጠበቅ አብረው የመጡ ደጅአዝማች ሺበሺ የሚባሉ አንድ የጋይንት ተወላጅ የሆኑ ሰው ነበሩ። ኋላ እንደገባኝ እርሳቸውም በጉዳዩ ትስማምተው ነበር። ለዚህም ማስረጃ አድርጌ የማስታውሰው አንድ ቀን ተጠርቼ ሁለቱ ራስ አያሌውና ደጅአዝማች ሺበሺ ብቻ ባሉበት ገባሁና ራስ አያሌው ብሩ «ይህ ልጅ ወድቆ እንዳይቀር እርስዎ ባልደረባ ሆነው እንዲያስታውሱት አደራ» ብለው ሰጡኝ። ከመግባቴ በፊትም የተነጋገሩበት ይመስለኛል። ደጅአዝማች ከአጠገባቸው እንዳልጠፋ ነግረውኝ ስወጣ እኔ ደግሞ በበኵሌ ለሌላ ሰው አሽከርነት የሰጡኝ መስሎኝ ተቆጠቼ ነበር የወጣሁት። ታዲያ ብዙኅም ሳንቆይ ግምጃ ቤቱ እንዲዘረፍ ታዘዘና ሠራዊቱ የመሰለውን ይዘርፍ ጀመር።
የግምጃ ቤቱ ሹም በእናቴ በኩል አማቻችን ስለሆኑ በየጊዜው ስኳር እንደ ልቤ ይሰጡኝ ስለነበር ፣ የስኳር ትልቅ አመለኛ ስለሆንኩ ያ የምወደው ስኳር ሲዘረፍ አየሁትና እኔም የዘረፋው ተካፋይ ሆንኩና ባለችኝ አንድ ስስ ጋቢ ስኳሬን ቋጠርኩና የጉዞውን አዋጅ ስጠባበቅ ወደ ማታ ገደማ ጉዞው ተጀመረ። እኔም ቋጠሮዬን ተሸክሜ ጉዞየን ቀጠልኩ። የምንሄደው ወደ ትንሣኤ አካባቢ ስለነበረ እኔም አብሬ ስጓዝ ጊዜው እየጨለመ መጣና ቋጠሮ ተሸክሜ መሄዱም እያቃተኝ ወደ ኋላ እጐትት ጀመር። በቀኝ በኵል የበለሳ ጦር ደርሶ ስለነበረ ከአንድ ጐድጓዳ ቦታ ላይ ብቻየን ሳዘግም አግኝቶ ጋቢየንና ስኳሬን ነጥቀው ጓዜን አቀለሉልኝ። ራሴን ትልቅ አድርጌ ስለምገምት በመደፈሬና ስኳሬም በመወሰዱ ያዘንኩ ፈጠን ባለ ሁኔታ መራመድ ጀመርኩ። ትንሣኤ ለመድረስ የተቃረብን ቢሆንም ሀገሩ ደጋ በመሆኑ ብርዱ በጣም ጐዳኝ በመሠረቱ ከሠራዊቱ እኔ የመጨረሻው የነበርኩ ይመስለኛል። ብርዱ አልበቃ ብሎ እንቅልፍና ድካም አንጓለለኝ። ሳላውቀው ስንደዶ ተንተርሼ ተኝቻለሁ። ጥሎ የማይጥለው አማላክ የደጅአዝማች መርሶ አያሌው ጦር ደጀን ሆኖ ከኋላ ይመጣ ስለነበር የእርሳቸው አሽከር የሆነ በለጠ የሚባል የእናቴ ዘመድ ቀድሞ ይጓዝ ስለነበር እኔ ከተኛሁበት ቦታ ሌሎች ሰዎች ቀድመው ደርሰው አንድ ልጅ ከዚህ ተኝቷል ብለው ሲናገሩ እኔ መሆኔን ሳይጠራጠር ፈጥኖ ደርሶ ስላነሣኝና ከአጋሠሥ ላይ ጭኖ ይዞኝ በመጓዝ በማግሥቱ ራስ አያሌው ከሠፈሩበት ደጋ መረባ አብሬ ደረስኩ። ታሪኬም ተወራ ጋቢየም ስኳር ተቋጥሮበት መቀማቴ ተሰማ ሌላ ጋቢ ተሰጠኝ ሰውነቴ ተቈራርጦ ለብዙኅ ቀን መነሣት አቃተኝ። ቢሆንም የአርበኝነቱ ሥራ የተጀመረ ስለሆነ ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀሴ የማይቀር በመሆኑ ያደረ የዋለ የመንገዱን ጉዳይ እላመደው ጀመር። ለምን እንደዚህ ደካማ ሆንክ የሚል ጥያቄ ሰው ያነሣ ይሆናል። አዎ መልሱ ሞልፋጣ ፣ አስተዳደግ ማለት ከበቅሎ ጀርባ የማልወርድ ደካማ ሆኜ በማደጌ ነው።
ራስ አያሌው ብሩ የአርበኝነቱን ሥራ እንደጀመሩ ወደ አምባጊዮርጊስ አካባቢ ጉዞ አድርገው የኢጣሊያንን መንግሥት ደግፈው ተሰልፈው ከነበሩ የሀገሬው ሰዎችም ጋር ተዋግተው በድል አድራጊነት ተወጡት። ደባርቅ ላይ መሸጉ ለረጅም ጊዜ ከባድ ውጊያ በማካሄድ ላይ የነበረውን የኢጣሊያ ጦር ለመውጋት የጐንደር አርበኞች በብዝኃት ከበባ ማድረግ ጀምረው ስለነበር የራስ አያሌው ሠራዊትም በወቅን በኵል የነበረውን ግንባር አደረጉ። እኔም ወደዚሁ ቦታ አብሬ የመጣሁ ስለሆነ የአካባቢው ሕዝብ ከጦርነቱ በመሸሽ መንደሩን የተወ እህሉን በጉድጓድ የቀበረ ስለሄደ በአካባቢው የሠፈረው ሠራዊት ከባድ የኑሮ ችግር ገጥሞት ነበር። እኔንም ለሁለተኛ ጊዜ የረሃብ ችግር ገጠመኝ። አንዳንዶቻችን በየመንደሩ አካባቢ የተቀበረውን የእህል ጉድጓድ ለመፈለግ ዘንግ ይዘን መሬቱን በመውጋት ጉድጓድ ፍለጋ ስንደክም እንውል ነበር።
በዚህ ኑሮ ችግር በገጠመን ሰሞን እንግሊዞች በአይሮፕላን ልዩ ልዩ ዕቃ አምጥተው ከአየር ስለጣሉ ዕቃውን አስነሥተው ለማስረከብ ደጅአዝማች ወልደሥላሴ መሸሻ የሚባሉ ዘመዴ በብዙኅ ሠራዊት ታጅበው ሲመጡ ከመንገድ ላይ ስጫወት ስላዩኝ አስጠርተው አነጋገሩኝ። እንደአጋጣሚ የእኝህ ሰው መኖሪያ ቤት በዚህ አካባቢ ስለሆነ እርሳቸውና ሠራዊታቸውም በምግብ አልተቸገሩም ነበር። በዚያን ቀን ሲያዩኝ ረሃብ እንደጐዳኝ ተረድተው ያነጋገሩኝ ነገር “አጐትህ ከእኔ ጋር ስትሄድ ቢያዩህ ደስ ስለማይላቸው ቀድመህ ሂደህ ከዚያ ማዶ ከተራራው አጠገብ ከሚገኘው በር ላይ ብትጠብቀኝ ወስጄ አብረን አድረን በማግሥቱ ወሬው ሳይሰማ እመልስሃለሁ” ስላሉኝ የሆድ ጉዳይ ሆነና ከሚመለሱበት ጊዜ ቀድሜ ከበሯ ላይ ቈሜ ጠበቅኋቸውና አብሬ ሄጄ ታላቅ ድግስ ስከሰክስ አመሸሁ። ከንጋቱ ላይ የተኵስ ድምፅ በብዛት ተሰማ። ምክንያቱም በትክክል ባናውቀውም ጦርነት መነሣቱን በመገመት ደጅአዝማች ወልደሥላሴ መሸሻ ሠራዊታቸውን ይዘው አሠራ በሚባለው ወንዝ በኵል ደባርቅ የሚገኘውን የተከበበውን ጦር ለመውጋት ሲንቀሳቀሱ የእኔ ጓደኛ የሚሆን ወንድ ልጃቸውንና እኔን ከቤት እንዳንወጣ አዘው ሄዱ። ጥቂት ከቈየን በኋላ ልጃቸው ስላደፋፈረኝ እኛም ጕዟችንን ወደዚያው አደረግንና ከወንዙ አጠገብ ስንደርስ ሰልፋቸውን አሳምረው ወደ እኛ ከሚመጡ ባንዳዎች ጋር ፊት ለፊት ተገናኘን። እኛም ደንግጠን ወደ ኋላ ስንሮጥ ወታደሮቹ ልጆች መሆናችንን ተረድተው ይመስለኛል ሳይተኵሱብን በመቅረታቸው ወደ ቤታችን በደኅና ደረስን።
ኋላ እንደተረዳነው ደባርቅ የነበረው የኢጣሊያ ጦር በውድቅት ሌሊት ከሠፈሩ ለቆ በራስ አያሌው ብሩ ሠራዊት ላይ አደጋ ስለጣለ አርበኛውና ራስ አያሌው ብሩም በታላቅ ጀግንነት ሲዋጉ አድረው ቍጥሩ የበዛ ሕዝብ አልቆ በዚሁ ቀን ጦርነት ራስ አያሌው እግራቸው ተሰብሮ ሲማረኩ ፣ ደጅአዝማች መርሶ አያሌውና ደጅአዝማች ሺበሺ ሞተዋል በተረፈ ያለቀው ሕዝብ ቍጥር ሥፍር ስላልነበረው ኋላ የየወገኑን ሬሳ ለሚፈልገው ዘመድ ሁሉ አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። እንዲያውም የደጅአዝማች ሺበሺ አስከሬን የተገኘው ከአንድ ወርኅ በኋላ ነበር። ከላይ እንደገለጽሁት እንጀራ በልቼ አድሬ እንድመለስ በደጅአዝማች ወልደሥላሴ መሸሻ ተጋብዤ ከሠፈሩ በሌለሁበት ቀን ሌሊቱን አደጋው ሲደርስ የሚገርመውና የሚያስደንቀው አብረውኝ የሚያድሩት ወጣቶች አብዛኛው ማለቃቸው ነው። እኔ ግን በዚህ ተአምር ቅልውጥ ሄጄ ተረፍሁ።
ደጅአዝማች ወልደሥላሴ መሸሻ ሙሉውን ቀን ሲዋጉ ውለው ወደማታ አካባቢ ወደ ቤታቸው በተመለሱ ጊዜ የራስ አያሌው ብሩን መማረክና የሕዝቡን እልቂት በይፋ ስለተነገረ እኔ በዚህ ጊዜ ትልቅ ሽብርና ውዥንብር ስለተሰማኝ የማያቋርጥ ልቅሶዬን ተያያዝሁት። ደጅአዝማች ወልደሥላሴም በሁኔታው በጣም ስለተቸገሩ ራስ አያሌውና እርሳቸውም ለእኔ እኵል የአንድ ቅድመአያት ልጆች መሆናችንን ጠቅሰው ይህን ያህል መሸበር እንደማይኖርብኝ ለማፅናናት ከፍተኛ ጥረት አደረጉ። ሰሚ ግን አላገኙም። ሁኔታው በጣም ስላሳሰባቸው ሌላ ዘዴ ፈለጉ። የሰሜንን ጦር የሚመሩት ደጅአዝማች ነጋሽ ወርቅነህ የአያቴ የወንድም ልጅ ስለሆኑ የጦር አለቃውም ፊትአውራሪ በሪሁን አደመ የአባቴ ትልቅ ወንድም ልጅ ስለሆነ ወደ እነርሱ ቢልኩኝ መንፈሴ እንደሚረጋጋ አስበው ይህን እቅድ ነገሩኝ። ምንም እንኳ ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት ዘመዶቼን የማላውቃቸው ቢሆንም ሃሳባቸውን በደስታ ተቀበልሁት። እርሳቸው ወስዶ እንዲያስረክበኝ ከመልእክት ጋር ላኩኝ።
ከደጅአዝማች ነጋሽ ወርቅነህ የጦር ሠፈር ከሰዓት በኋላ ገደማ ስንደርስ የፊትአውራሪ በሪሁን አደመ ጦር ወደ ሠፈሩ ለመሄድ ሲጓዝ ፊት ለፊት ገጠመን። ይዘውኝ የሄዱት የደጅአዝማች ወልደሥላሴ የጦር አዛዥ ከመንገድ ላይ እጅ ሲነሡ ከደጅአዝማች ወልደሥላሴ ተልከው መምጣታቸውን ስለተናገሩ መልእክቱን እንዲናገሩ በቅሎውን ገቶ ሲቆም እርሳቸውም እኔን አስቀድሞ “የአጐትዎን ልጅ ዳኘው ወልደሥላሴ” ብለው ንግ ግራቸውን ሳይጨርሱ ከበቅሎቅ ፈጥኖ ወርዶ አቀፈኝ። ከራስ አያሌው ጋር መኖሬን ስለሚያውቅ ሞቷል ብሎ የገመተ ስለሆነ ተርፌ በመገኘቴ በጣም ተደሰተ። ጦሩ ገና ከደጅአዝማች ነጋሽ ወርቅነህ ሠፈር ሲወጣ በመገናኘታችን የእኔን መምጣት ለእርሳቸው ሳይነግር መሄድ ስላልፈለገ እኔንና ያመጡኝን ሰዎች ይዞ ገባና ደስታውን ነገራቸው። እርሳቸውም በታላቅ ደስታ ተቀብለው ሰዎቹን አመስግነው ከዚያ እንዳድር ጠየቁ። ፊትአውራሪ በሪሁን “የዛሬን ከእኔ ጋር አድሮ እንዲመጣ ይፍቀዱልኝ” ብሎ ጠይቆ ስለፈቀዱለት ጥቂት ካጫወቱን በኋላ ጉዞአችንን ቀጥለን ወደ ፊትአውራሪ በሪሁን ሠፈር ደረስን።
የጦር ሠፈር እያልሁ የምጠራው ሁሉ የሰዎች መንደር ነው እንጂ ጦሩ ሠርቶ የሠፈረበት አይደለም። አሁን የፊትአውራሪ በሪሁን ሠፈር ሆኖ ያገኘሁት እዚያ አካባቢ የታወቁ ሀብታም ሰው ከመሆናቸውም በላይ እኝህ ሰው ቀደም ብለው የፊትአውራሪ በሪሁንና የእኔን አክስት ወይዘሮ አያልነሽ ረታን አግብተው የነበሩ ሰው በመሆናቸው እርሳቸውም በታላቅ ደስታ ተቀብለው የምበላው በፍጥነት እንዲቀርብልኝና ያን የጐፈተውን ጠጕሬን ሊላጭ ሲሰናዱ የጠላት ጦር መጥቶ ከቃፈር ጦር ላይ አደጋ በመጣሉ ተኵስ ስለተሰማ ወዲያው ጥሩንባ ተነፍቶ በፍጥነት ጠላት ወደመጣበት በኵል ጉዞ ሲጀመር እኔም አብሬ ፊትአውራሪ በሪሁንን ተከትዬ መጓዝ ጀመርሁ። ከአንድ ዳገት ላይ ስንደርስ ፊትአውራሪ በሪሁን ወደ ኋላ ሲመለከት የእኔን መምጣት በማየቱ ተቆጥቶ ከመንደሩ ብዙኅ ያልራቅን ስለሆነ ተመልሼ እንድሄድ ሲያዘኝ የለበሰውን ኩታ አውልቆ ሰጠኝና ይዤ እንድሄድ አጥብቆ አዘዘኝ። ትእዛዙን ባልወደውም ጥቂት ከቆየሁ በኋላ የመትረየስ ተኳሾችና አጃቢዎቻቸው ስለመጡ አብሬ እንድሄድ ጋብዘው ወስደው እነዚህ መትረየስ ተኳሾች በአንድ ተራራ ላይ ሆነው መትረየሱን ሲያንኳኩት እጅግ ደስ ይል ነበር። የመትረየሶቹ አጃቢዎችና ጠባቂዎች የጦርነቱ መሟሟቅ ወኔያቸውን ስለገፋፋው ወደፊት ገሥግሠው ከእግረኛው ሠራዊት ጋር በመቀላቀላቸው ከመሸ በኋላ ወደ ሠፈር ለመሄድ ስንነሣ ጓዙን ማለት የጥይቱን ሣጥኖች የሚሸከም በመጥፋቱ የተቸገርን ቢሆንም እኔም ጭምር የሸክሙ ተካፋይ ሆኘ ጉዟችንን ብንጀምርም ዘማቹ ጦር ፊትአውራሪ በሪሁን ጭምር ወደ ሠፈር ገብተው ሲቆጣጠሩ እኔ እንግዳውና መትረየሶቹም ተመልሰው ባለመግባታቸው ትልቅ ሽብር ተፈጠረና ጦሩ እንደገና ወደ ኋላ ተመልሰው ወደ እኛ ሲመጣ ከመንገድ አገኘነውና ታላቅ ደስታ ሆነ። ፊትአውራሪ በሪሁን በመጀመሪያ በተገናኘንበት ቀን እንደዚህ ያለ ችግር በመፈጠሩ መቆጣቱ በግልጽ ቢታይም ምንም አልተናገረኝም። በጦር ግንባር መዋል የተለማመድሁ ቢሆንም በዛሬው ቀን ግን መትረየስ ተኳሾች የአለቃቸው ወንድም መሆኔን በመረዳት ብዙኅ ጥይት እንድተኵስ በማድረጋቸው ተደስቼ ነው የዋልሁት።
ከፊትአውራሪ በሪሁን ጋር ሦስት ቀን ያህል ከቆየሁ በኋላ እርሱ ከጦር ግንባር ስለሚሠፍር አደጋ እንዳይደርስብኝ ወደ ደጅአዝማች ነጋሽ ወርቅነህ ሠፈር እንድሄድ ተደረገ። ቀደም ብሎ ከራስ አያሌው ብሩ ሠፈር ወደ ወንድሙ ሄዶ የነበረው የፊትአውራሪ በሪሁን አደመ ትንሽ ወንድም በዝኀብህ አደመን ከዚሁ አገኘሁትና የማውቀው ዝመድ በማግኘቴ ተደሰትሁ። ቢሆንም እንድንጓጓዝበት የተሰጠችን አንዲት በቅሎ ስለነበረች እርሱ እንደትልቅነቱ ከኮረቻው ላይ ይቀመጥና እኔ እየተፈናጠጥኩ እንጓዛለን። በቅሎ የሚይዝ ሰው ያልተሰጠን ስለሆነ ጉዟችንን ጨርሰን ከሠፈር ስንደርስ በቅሎይቱን እንድስብና እንዳራግፍ ያዘኛል። እኔም ይህን ትእዛዝ የማልቀበል በመሆኔ በሁለት ወንድማማች መካከል የማይታረቅ ጠብ ተጀመረ። እኔ ተፈናጥጬ አቀብት በምንወጣበት ጊዜ አውቆ ባልሆነ መንገድ የሄደ ይጥለኝ ነበር። አንድ ቀን ሊመታኝ ሲያባርረኝ አንድ ውኃ ያለበት ጭቃ መሬት በመርገጤ ውኃውና ጭቃው ተፈናጥሮ ልብሱን ስላበላሸበት በጣም ተናዶ ይህ “የደበሎ ለባሽ ልጅ” ብሎ ስለሰደበኝ በጉዳዩ ተቆጥቼ ልቅሶ ጀመርሁና ወደ ደጅአዝማች ነጋሽ ወርቅነህ አዳራሽ ገብቼ በማልቀስ ላይ መሆኔን ተመልክተው ምክንያቱን ሲጠይቁኝ “በዝኀብህ የአጐዛ ለባሽ ልጅ” ብሎ ሰደበኝ የሚል ክሴን ሳቀርብ አጐዛ ለባሽነት የሰሜንን ትውልድ ስለሚመለከት እርሳቸውም ጭምር መሳደቡ መሆኑ ተሰማቸው መሰል ተቆጥተው እንዲገረፍ አዘዙ። ቢሆንም ወዲያው ተወስዶ ገረፍነው ብለው ሳይነኩ የመለሱት ይመስለኛል።
ጭቅጭቃችን የቀጠለ መጥቶ በራም ስለተቸገርሁ አንድ ቀን ሸዋዳ ከሚባለው ቆላማ ቦታ ተነሥተን ወደ ወገራ ከወጣን በኃላ ፊትአውራሪ በሪሁን ሁልጊዜ ግንባር ሠፋሪ ስለሆነ ወደፊት ሲጓዝ እኔ ተደብቄ አብሬ ስሄድ ቆይተን ሠፈር ስንደርስ ለካስ ባለሀገሩ አምጦ ኑሮ ጦርነት ሊገጥመን ተዘጋጅቶ ስለነበር ወደማታ ገደማ ተኵስ ከፈተብን። ያን የመጣንበትን መንገድ እንደገና ስንጓዝ አምሽተን ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ገደማ ወደ ደጅአዝማች ነጋሽ ሠፈር ደረስን ከበባው ቀጥሎ ሦስት ቀን ተዘግተን ከተቸገርን በኃላ በሦስተኛው ቀን በተዋጊዎቹ መካከል ሽምግልና ተካሄዶ ሠራዊቱ ወደ መንደር ሳይገባ ወደ ቦዛ እንዲሄድ ከስምምነት ላይ ተደርሶ በዚሁ መንገድ ወገራን አቋርጠን ወደ እንግሊዞቹ ሠፈር ቦዛ ደረስን። ምግብ ከቀመስን ሦስት ቀን አልፎናል። አሁን የደረስንበት አካባቢ ለፊትአውራሪ በሪሁንና ለእኔም የዘመድ ሀገር በመሆኑ በምግብ በኵል ችግራችን የተቃለለ ቢሆንም የአክስታችን ባለቤት ፊትአውራሪ ከበደ በላይ ደግሞ ከደጅአዝማች ነጋሽ ወርቅነህ ጋር ቅያሜ ፈጥረው ስለነበር ወደ ዛሬማ በመጓዝ ላይ ሳለን አደጋ ይጥላል ተብሎ ስለተወራ በረሃብ የተጐዳው ሠራዊት በፍርሃት ተውጦ ነበር። ቢሆንም ፊትአውራሪ ከበደ በላይ ነገሩን አመዛዝኖ የልጆቹን አጐቶችና ወንድሞች መፍጀት ተገቢ አለመሆኑን በማመዛዘን በሰላም አሳለፈን። ዛሬማ ስንደርስ የመስለኛል ደጅአዝማች ነጋሽን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጠርተዋቸዋል ተብሎ እንግሊዞች ባቀረቡት ሁለት ፎርድ ትልልቅ መኪናዎች ኀምሣ ከሚሆኑ ሰዎች ጋር ወሰዷቸው።
ደጅአዝማች ነጋሽ ወርቅነህ ከመሄዳቸው በፊት እንደራሴያቸው ፊትአውራሪ በሪሁን አደመ መሆኑን ለሠራዊታቸው አውጀው ስለሄዱ ቀሩው ሠራዊት ወደ ሰሜን ተጉዞ ደረስጌ ማርያም ለመድረስ ጥቂት ሲቀረን “በነጋሽ አምላክ ቁም” የሚል ድምፅ ከባለሀገሩ ሰማን። በእኛም በኵል የደጅአዝማች ነጋሽ ሠራዊት መሆናችንን ሰዎች ስለገለጹ እነዚያም ቁም የሚል ትዕዛዝ የሰጡት የሕዝብ ጦር ደጅአዝማች ነጋሽ የት እንዳሉ ስለጠየቁ መንግሥት ጠርቶ የወሰዳቸው መሆኑን ከተገለጸላቸው በኋላ የደጅአዝማች ነጋሽ አለመኖርን ሲያረጋግጡ ተኵስ ጀመሩ። በመሰረቱ የደረስጌ ሕዝብ በደጅአዝማች ነጋሽ ሠራዊት ላይ ከፍተኛ ቂም ስለነበረው ለመበቀል አቅዶ ያደረገው ውግያ ነበር።
ፊትአውራሪ በሪሁን ሽዋዳ የቀሩ መትረየሶች ለማምጣት ወደዚያ ሄዶ ስለነበረ የቀረው ሠራዊት ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ገደማ ድል ተመቶ ዝርፊያ ተጀመረ። እኔ ከዘራፊው ጦር መስዬ ላይና ታች ስለ አምሽቼ ወደ መጨረሻው የጨነቀኝ ስለመጣ ሳላውቀው ማልቀስ ስለጀመርሁ ተጋለጥሁና የዘራፊዎቹ ተከታዮች በእድሜያቸው እኔን የሚመስሉ ልጆች ስላዩኝ ማባረር ጀመሩ። ከቤተክርስቲያኑ አጥር ግቢ ውስጥ ገፈፋውና ዝርፊያው ይካሄድ ስለነበረ ወደ ዚያው ዘልዬ ወደ ቅጥር ግቢው ስገባ ልጅ መኰንን ጋረድ የሚባል የድጅአዝማች በላይ ገብረመድኅን የልጅ ልጅ ሀገሬው ማንነቱን ደኅና አድርገው ስለሚያውቁና ተገቢውንም ክብር በመስጠት መሳሪያውና ትጥቁ እንዳይነካ የተወሰኑ ሰዎች የጠበቁት ከቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ከሚገኘው ቤት ውስጥ ከበራፋ ላይ ቆሞ ውጭውን ይመለከት ስለነበረ እኔ የተባረርሁ ስመጣ ያየኝና ወጥቶ አቅፎ ይይዘኛል።
እርሱን ሳገኝ ልቅሶዬ በዝኀ ከእርሱም ላይ ተጠመጠምሁ። እርሱም ለሚጠብቁ ሰዎች ማንነቴን ስለነገራቸው ሰዎቹም ተደንቀው ከእርሱ ጋር እንድጠበቅ አደረጉ። በዚያን ቀን የተማረከው ሰው ሁሉ ልብሱንም ተገፎ በዚያ ብርድ የተንቀጠቀጠ ተሰልፏል። ልብስ ሳንገፈፍ የቀረነው ሁለታችን ብቻ ስንሆን እኔ አጋጣሚ ነው እንጂ ማንነቴ አልታወቀም ነበር። ሕዝቡንም በጣም የአስገረመው ደግሞ የእኔ ልብስ ሳይገፈፍ መቅረቱ ነው። በመሠረቱ ልጅ መኰንን ጋረድ የራስ ገብረመድኅን የልጅ ልጅ በመሆኑ እንዳይገፈፍ ሲወሰንለት እኔ ግን ምንም እንኳን እንደርሱው የራስ ገብረመድኅን የልጅ ልጅ መሆኔ ሕዝቡ ሳያውቅ ከነልብሴ መገኘቴ ሌላ ተአምር ሆኖ ነው የታየው። * እንዲያውም ከመደነቃቸው ብዝኀት እነዚያ የሰሜን ባላባቶች ናቸው የሚባሉት ሰዎች አምላክ ምንጊዜም ሲጠብቃቸው እንደሚኖር አድርገው ነው የገመቱት።
ከዚህ ጦርነት ፊትአውራሪ በሪሁን አደመ በድል አድራጊነት ወደ በየዳ የተሻገረ ስለሆነ ጥቂት ቀናት ደረስጌ ከቈየሁ በኋላ እኔም ወደ በየዳ ተሻግሬ ከአጐቴ ልጅ ጋር በሰላም ስለተገናኘሁ ለዋሬ ወደ ሚባለው ገዳም ሄጄ ትምህርቴን ቀጠለሁ። ለዋሬ የምማረው ከፊትአውራሪ በሪሁን እናት ከወይዘሮ ደብሪቱ ንጉሤና ከፊትአውራሪ አዳል ወርቅነህ ጋር ሆኜ ስለነበረ ጧት ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዴ በፊት ወደ ማዕድቤቱ የሄድሁ እሳት እሞቃለሁ። ቀጥሎ ቁርስ በልቼ ስለምሄድ ማዕድቤቱ በጣም ትልቅ ስለሆነ በልዩ ልዩ ምክንያት የሚታሰሩ ሰዎች ከዚያው ስለሚገኙ ጧት ጧት በሄድሁ ቍጥር ሕልም ሲፈቱና ሲናገሩ እሰማለሁ። አንድ ቀን እኔም ሕልም አየሁና ጉዳዩ ማንን እንደሚመለከት ሳልነግር “ሁለት ወንድማማቾች ተጣልተው እናቲቱ ለአንዱ አብረው አንዱን ሲመቱት አየሁ” ብዬ ንግግሬን እንደጨረስሁ አንዱ እስረኛ ቀበል ብሎ መፍትሐት ጀመረና እናቱ የመቱት ልጅ ሞቷል ሲል ሕልሙን ፈትሐው። የተጣላነው እኔና ትንሹ ወንድሜ ነበርን። ሲመታም ያየሁት እርሱን ስለሆነ ከዚያን ቀን ጀምሮ ልቅሶ ጀመርሁ። እውነትም ትንሽ ወንድሜንና እናቴን ጐንደር ጥያቸው የመጣሁ ስለሆነ የእንግሊዝ አውሮፕላን ጐንደርን ሲደበድብ ሕዝቡ ወደ ደፈጫ ኪዳነ ምሕረት ወደ ሚባለው ቦታ ይሸሽ ስለነበረ እናቴና ወንድሜ አብረው ሸሽተው ሳሉ አውሮፕላን ደርሶ ሲደበድብ ትንሽ ወንድሜ ተገድሎ ኑሯል።
እናቴም አንዱ ልጃቸውን ጐንደር ከቀበሩ በኋላ ከጦርነቱ ውስጥ የነበርሁት ልጃቸው እንደሞትሁ ገምተው በየቦታው ሲንከራተቱ ራስ አያሌው ብሩ በተማረኩበትና ሕዝብ ባለቀበት ቀን ከደጅአዝማች ወልደሥላሴ መሸሻ ጋር ወጥቼ መትረፌን ሲሰሙ ወደዚያው ሄደው ሲጠይቁ ከደጅአዝማች ነጋሽና ከፊትአውራሪ በሪሁን ጋር በደኅና መገናኘቴን ሲያረጋግጡላቸው አስከፊ የሆነውን የሰመንን ጉዞ ጀምረው ወደ ፊትአውራሪ በሪሁን ሠፈር ሲደርሱ እናትህ መጥተዋልና እንድትመጣ የሚል መልእክተኛ መጣ። ቀይ ልጅ አብሯቸው እንዳለ ብጠይቅ አለመኖሩን ነገረኝ። ልቅሶዬን ቀጠልሁና እናቴን ለማየት እንደማልፈልግ ተናግሬ አልሄድም ብዬ ቀረሁ። ሊወስዱኝ የመጡ ሰዎች ተመልሰው ሁኔታውን ሊገልጹ እናቴ ራሳቸው ለመምጣት ጉዞ ይጀምራሉ። ከዚህ እኔ ካለሁበት ደግሞ ወይዘሮ ደብሪቱና ፊትአውራሪ አዳል ወርቅነህ ባደረግሁት ስህተት ወቅሰው እናቴን ሄጄ እንዳይ አስገድ ደው ይልኩኛል። ከግማሽ መንገድ እርሳቸው ሲመጡ እኔ ስሄድ ተገናኘን። ልቅሶዬን አላቋርጥም ብዬ በጣም አስቸገርሁ። ታስቦ የነበረው እኔ ከለዋሬ እንደመጣሁ የወንድሜን ሞት ከሰማሁ አብሬያቸው እንደማልሄድ ጠርጥረው መርዶው መነገሩ ቀረና ወንድሜ ጐንደር መቅረቱን ደጋግመው በመነገር ሊያሳምኑኝ ሞከሩ። አንድአንድ ጊዜ ተስፋ ሳድርግ አብዛኛውን ጊዜ የዚያን ሕልም ፍቺ ልረሳው አልቻልሁም። ቢሆንም ወደ ጐንደር ጉዞ ቀጥለን ትንሣኤ ከሚባል ቦታ ስንደርስ ያሳደገኝና በጣም የምወደው ፊትአውራሪ ገብረሥላሴ ዘረፋ የሚባል ዘመዴ መሞቱን ሰምቼ ልቅሶ ለመድረስ ምሽቱ ወደምትገኝበት መንደር ሄደን ያላቀሰን ስንገባ ዘመዶቹ ተሰባስበው ጠብቀውን ስለነበረ የሰማሁ መስሏቸው የወንድሜንም ስም ያነሡ ያለቅሱ ጀመር። መርዶው ከዚሁ ትፈጸመ። ብዙኅ ችግር ደርሶብኛል። ሆኖም በሕይወቴ እንደ ወንድሜ ሞት ያሳዘነኝ ነገር የለም።
ከዚህ ቁርጡን ካወቅሁ በኋላ ጐንደር መግባቴ ግድ ነበርና ጉዟችንን ቀጥለን ጐንደር ደረስን። በዚያን ጊዜ ልዑል አልጋወራሽ መርዕድ አዝማች አስፋው ወሰን የጐንደር ክፍለ ሀገር ገዢ ሆነው መጥተው ስለነበረ አርበኛ ሁሉ የድካሙን ዋጋ ለማግኘት በብዛት ጐንደር ገብቶ ደጅ ጥናቱን ተያይዞት ነበርና እኔም ከሕፃንነት እድሜ ጀምሮ መተዳደሪያዬ የነበረው ሀገር እንዲሰጠኝ ለደጅ ጥናት ተሰለፍሁ። ወደ አልጋወራሹም ለመቅረብ ጊዜ አልወሰደብኝም ምክንያቱም በአካባቢው የሚገኘው መኳንንት አብዛኛው የሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑ የምረዳበት መንገድ ለማግኘት የሁሉንም ትብብር አላጣሁም። እኔም ወደ ልዑልነታቸው ቀርቤ ሳስረዳ አነጋገሬ በጣም የጐላ ደፋር ስለነበርሁ ልዑልነታቸውም ጊዜ ሳይወስዱ ወደ ትምህርት ቤት እንድገባ የወርኅ ደመዎዝም እንዲሰጠኝ በማዘዛቸው በዚህ ውሳኔ ሳልረካ ቤተሰብኤን የት አስቀምጣለሁ የሚል ጥያቄ በማቅረቤ ግዛቱ እንዲሰጠኝና እኔ ግን ከላይ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ወደ ትምህርት ቤት እንድገባ ደመዎዙም እንዲሰጠኝ ማዘዣ ወጣ። ተገድጄ ካልሆነ በስተቀር በዚያን ጊዜ ስለትምህርት ጥቅም እኔ ዋጋ አልሰጠሁትም። ግን ማዘዣ ይዤ ወደ ወገራ አውራጃ ሄጄ ከዚያም የአውራጃ ገዢ ደጅአዝማች ነጋሽ ወርቅነህ ስለሆኑ በተፋጠነ ሁኔታ ትዕዛዙ ተላለፈልኝና ወደ ቦታው ስወርድ ያን ለእኔ የተሰጠው መተዳደሪያ ቀደም ብሎ በአበጋዙ በኵል ለአሥራ ስድስት አርበኞች የተመደበ ስለሆነ ይገባናል የሚሉት ሰዎች በባላጋራነት ተነሥተው ጉዳዩ ዳባት ለሚገኙት ገዢ ተመራና ለፍርድ ቀረበ። ጊዜ ሳይወሰድ ከልዑልነታቸው የተሰጠው ውሳኔ እንዲከበር ተፈረደና ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ቆላው ከመሄዴ በፊት ጐንደር የሚገኙትን እናቴን ለማነጋገር ሄድሁ።
እናቴ ግን ሁኔታውን በቅርብ ይከታተሉ ስለነበረ ከከፍተኛ ሃሳብ ውስጥ ገብተው ኑረው ሁኔታውን ለእኔ ሳይገልጹ ወደ ሀገራቸው ጋይንት ለመሄድ መነሣታቸውን ነግረውኝ ከዚያው ጐንደር ቆይቼ እንድሸኛቸው ጠየቁኝ። እንዲያውም ለጊዜው ወደ ሀገራቸው መሄዳቸው ለእኔ አመች እንደሚሆን ገምቼ ተስማማሁና ከዚያው የሚሄዱበትን ቀን መጠባበቅ ጀመርሁ። ደጅአዝማች ታደሰ ይማም የሚባሉ የሀገራቸው ሰው ተሹመው በአንድ ትልቅ ፎርድ መኪና ጓዛቸውንና አሽከሮቻቸውን ጭነው ስለሚሄዱ እኔም አብሬ እንድሄድ ቦታ ትይዞልኛል ብለው ነገሩኝ። ለካስ እናቴ የገጠማቸውን ችግር ለደጅአዝማች ታደሰ ይማም አስረድተው አዘዞ ድረስ አብሬ ወርጄ ሸኝቼ እንድመለስ ስለጠየቁኝ ምንም ሳልጠረጥር ከዚያ ፎርድ መኪና ተሳፍሬ አዘዞ ስንደርስ ለመውረድ ስሞክር የደጅአዝማች ታደሰ ሰዎች ባለሁበት እንድቀመጥ አስገድደው ጉዟቸውን ቀጠሉ። በመረረ ሁኔታ ብጮህ ባለቅስ የሚያስጥለኝ አላገኘሁም። አሁን እናቴ ባደረሁት ትግል ማዘናቸው ባይቀርም እንዳትሞትብኝ ብዬ ያደረሁትን ሁኔታውን ተረዳልኝ በማለት እርሳቸውም ብዙኅ ይናገሩ ጀመር። እንዲሁ ያለቀስሁ ቁልቋል በር ከሚባለው ትንሽ ከተማ ስንደርስ ብዙኅ የባለሀገር ወታደር ከተማይቱን አጥለቅልቆት አገኘን። የማን ሠራዊት መሆኑን ሲጠይቁ የደጅአዝማች አምባቸው ገሠሠ ጦር መሆኑን እናቴ ሲሰሙ በጣም ደነገጡና እኝህ ሰው የራስ ገብረመድኅን የወንድም የልጅ ልጅ መሆናቸውን ስለሚያውቁ ይህ ልጅ ከተለቀቀ ሄዶ ይናገርና ችግር ይፈጠራል በማለት ተናግረው እንደተያዝሁ በአንድ ክፍል ተዝግቼ አደርሁ። ደጅአዝማች አምባቸው ገሠሠም ወደ ሸዋ በእግር የተጓዘ ስለነበር ሌሊቱን ተነሥተው ተጉዘዋል። እኝህ ሰው አዲስ አበባ ሳይደርሱ ዋድላ አካባቢ ታመው መሞታቸውን ቆይቼ ሰማሁ።
በዚህ ሁኔታ ተይዤ ደብረ ታቦር ደረስን። ለማምለጥ ብዙኅ ሞክሬ ሳይሳካልኝ ጋይንት ውስጥ ቤተልሔም ወደሚባል ከዚህ በፊት በኢጣሊያ ጊዜ ተርበን ወደ ሄድንበት ቦታ ይዘውኝ ገቡ። ጥበቃውም ያላቋረጠልኝ ቢሆንም ከዚያ ተነሥቼ ከድቼ ለመሄድ ከባድ ነበር። አንድ ዓመት ያህል ከዚያው ከቆየሁ በኋላ ልዑል አልጋወራሽ ድብረ ታቦርን ለመጐብኘት የሚመጡ መሆናቸው ተሰማና የእናቴ ወንድሞቿ ለመሄድ በመዘጋጀት ላይ ስለሆኑ አብሬ ሄጄ እንድመለስ እናቴን ለመንሁ። በተለይ የእናቴ ትንሽ ወንድም ግራአዝማች ወንዳውክ ተድላ ይህ ልጅ ከሄደ ሊመለስ ስለማይችል በእኔ ኃላፊነት አልወስድም ብሎ መወሰኑን አስታወቀ። የእናቴ አክስት ልጅ ፊትአውራሪ በየነ ንጉሤ የአቀረቡት ሃሳብ ደግሞ ተመልሼ እመጣለሁ ብዬ የእናቴ ጡት ከመታሁ ከእርሳቸው ጋር ሊወስዱኝ ፈቃደኛ መሆናቸውን አረጋገጡ። መሐላውን ተቀብዬ የእናቴን ጡት መታሁና በልቤ ግን እግዚአብሔር እንዳይመልሰኝ በማለት ተማመንሁ። በዚሁ መሠረት ከፊትአውራሪ በየነ ንጉሤ ጋር ተጉዤ ደብረ ታቦር ደረስን። ከሁሉም ቀድሜ ወደ አልጋወራሽ መቅረብ ስለቻልሁ የገጠመኝን ችግር በዝርዝር ሁኔታውን በማስረዳቴ ወዲያውኑ ባልደረባ ተሰጠኝና ከዚያን ቀን ጀምሮ በሠፈራቸው ቦታ እንዲሰጠኝና ከዚያው እንድቆይ ተፈቀደልኝ። ታዲያ ወደ ግቢው እንደልቤ ስገባና ስወጣ የሚያውቀኝ ሰው ሁሉ የተገረመ ስልእኔ ብዙኅ ይወራ ጀመር። አልጋወራሽ ደብረ ታቦርን ለቀው የሚሄዱበት ቀን ፈጽሞ ምሥጢር ስለነብር ከዚያው ከግቢው ያደርሁ ከመጠባበቅ ላይ ሳለሁ አንድ ቀን ወደ ማታ የፊትአውራሪ በየነ ንጉሤ ሠራተኞች ወደ ግቢው መጥተው ፈልገው አገኙኝና የፊትአውራሪ የጭን በቅሎ ሸህሊት መጥፋቷን ስለነገሩኝ ደንግጬ ከእነርሱ ጋር ሆኜ ሌሊቱን በሙሉ የደብረ ታቦርን አካባቢ ስንዞር አድረን ወደ ጧት አካባቢ ወደ ጐንደር በሚወስደው መንገድ ስንዘዋወር ጩኸቴን ለቀቅሁት። የሸህሊት መጥፋት የእኔን ዕድል አሰናከለችውና ሳለቅስ ውዬ ከፊትአውራሪ በት አደርን። እነርሱ የመሰላቸው ለእናቴ በማልሁት መሠረት የቀረሁ መስሎአቸው ተደሰቱ። በቅሎዋም ሳትገኝ ቀረች እኛም ተመልሰን ወደ እናቴ ሄድን በአልጋወራሽ ግቢ ስለተደረገልኝ የክብር አቀባበል በሰፊው ይወራ ጀመር። እናቴም ተመልሼ በመምጣቴ ከልብ መረቁኝ።
አልጋወራሽ ከዚያን ጊዜ ጀምረው ወደ ወሎ ጠቅለው የሄዱ መሰለኝ። ወዲያው ራስ እምሩ የጐንደር ገዢ ሆነው ስለተሾሙ አርበኛው ሁሉ ወደ ጐንደር በመሄድ የመተዋወቅና ሹመትም ያላገኘው ሹመት የመጠየቅ ልምድ ስለንበረ አሁንም እነዚያው ዘመዶቼ ወደ ጐንደር ለመሄድ ሲነሡ በአሁኑ ጊዜ የእናቴ ትንሽ ወንድም ባለፈው አልወስድህም በማለቱ መቀየሜን በማስታወስ እንዳልቀር የእናቴን ጡት መትቼ አብሬው እንድሄድ አስፈላጊው ዝግጅት አልቆ ጉዞ ጀመርን። ጐንደር ደረስን። ራስ እምሩ የጐንደርን ሕዝብ በደስታ የሚመለከቱት አይመስልም። እንዲያውም ነጠላ የቀማውን ሁሉ ሰቀለ ፣ ቀማኛ አጠፋ የተባለም ተነገረላቸው። ሽፍታው ግን ጐንደርን ሊወራት ተቃርቦ ነበር። ብዙኅ ሳይቆዩ ተሽረው አሜሪካ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ።