ከዚህ ቁርጡን ካወቅሁ በኋላ ጐንደር መግባቴ ግድ ነበርና ጉዟችንን ቀጥለን ጐንደር ደረስን። በዚያን ጊዜ ልዑል አልጋወራሽ መርዕድ አዝማች አስፋው ወሰን የጐንደር ክፍለ ሀገር ገዢ ሆነው መጥተው ስለነበረ አርበኛ ሁሉ የድካሙን ዋጋ ለማግኘት በብዛት ጐንደር ገብቶ ደጅ ጥናቱን ተያይዞት ነበርና እኔም ከሕፃንነት እድሜ ጀምሮ መተዳደሪያዬ የነበረው ሀገር እንዲሰጠኝ ለደጅ ጥናት ተሰለፍሁ። ወደ አልጋወራሹም ለመቅረብ ጊዜ አልወሰደብኝም ምክንያቱም በአካባቢው የሚገኘው መኳንንት አብዛኛው የሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑ የምረዳበት መንገድ ለማግኘት የሁሉንም ትብብር አላጣሁም። እኔም ወደ ልዑልነታቸው ቀርቤ ሳስረዳ አነጋገሬ በጣም የጐላ ደፋር ስለነበርሁ ልዑልነታቸውም ጊዜ ሳይወስዱ ወደ ትምህርት ቤት እንድገባ የወርኅ ደመዎዝም እንዲሰጠኝ በማዘዛቸው በዚህ ውሳኔ ሳልረካ ቤተሰብኤን የት አስቀምጣለሁ የሚል ጥያቄ በማቅረቤ ግዛቱ እንዲሰጠኝና እኔ ግን ከላይ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ወደ ትምህርት ቤት እንድገባ ደመዎዙም እንዲሰጠኝ ማዘዣ ወጣ። ተገድጄ ካልሆነ በስተቀር በዚያን ጊዜ ስለትምህርት ጥቅም እኔ ዋጋ አልሰጠሁትም። ግን ማዘዣ ይዤ ወደ ወገራ አውራጃ ሄጄ ከዚያም የአውራጃ ገዢ ደጅአዝማች ነጋሽ ወርቅነህ ስለሆኑ በተፋጠነ ሁኔታ ትዕዛዙ ተላለፈልኝና ወደ ቦታው ስወርድ ያን ለእኔ የተሰጠው መተዳደሪያ ቀደም ብሎ በአበጋዙ በኵል ለአሥራ ስድስት አርበኞች የተመደበ ስለሆነ ይገባናል የሚሉት ሰዎች በባላጋራነት ተነሥተው ጉዳዩ ዳባት ለሚገኙት ገዢ ተመራና ለፍርድ ቀረበ። ጊዜ ሳይወሰድ ከልዑልነታቸው የተሰጠው ውሳኔ እንዲከበር ተፈረደና ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ቆላው ከመሄዴ በፊት ጐንደር የሚገኙትን እናቴን ለማነጋገር ሄድሁ።
እናቴ ግን ሁኔታውን በቅርብ ይከታተሉ ስለነበረ ከከፍተኛ ሃሳብ ውስጥ ገብተው ኑረው ሁኔታውን ለእኔ ሳይገልጹ ወደ ሀገራቸው ጋይንት ለመሄድ መነሣታቸውን ነግረውኝ ከዚያው ጐንደር ቆይቼ እንድሸኛቸው ጠየቁኝ። እንዲያውም ለጊዜው ወደ ሀገራቸው መሄዳቸው ለእኔ አመች እንደሚሆን ገምቼ ተስማማሁና ከዚያው የሚሄዱበትን ቀን መጠባበቅ ጀመርሁ። ደጅአዝማች ታደሰ ይማም የሚባሉ የሀገራቸው ሰው ተሹመው በአንድ ትልቅ ፎርድ መኪና ጓዛቸውንና አሽከሮቻቸውን ጭነው ስለሚሄዱ እኔም አብሬ እንድሄድ ቦታ ትይዞልኛል ብለው ነገሩኝ። ለካስ እናቴ የገጠማቸውን ችግር ለደጅአዝማች ታደሰ ይማም አስረድተው አዘዞ ድረስ አብሬ ወርጄ ሸኝቼ እንድመለስ ስለጠየቁኝ ምንም ሳልጠረጥር ከዚያ ፎርድ መኪና ተሳፍሬ አዘዞ ስንደርስ ለመውረድ ስሞክር የደጅአዝማች ታደሰ ሰዎች ባለሁበት እንድቀመጥ አስገድደው ጉዟቸውን ቀጠሉ። በመረረ ሁኔታ ብጮህ ባለቅስ የሚያስጥለኝ አላገኘሁም። አሁን እናቴ ባደረሁት ትግል ማዘናቸው ባይቀርም እንዳትሞትብኝ ብዬ ያደረሁትን ሁኔታውን ተረዳልኝ በማለት እርሳቸውም ብዙኅ ይናገሩ ጀመር። እንዲሁ ያለቀስሁ ቁልቋል በር ከሚባለው ትንሽ ከተማ ስንደርስ ብዙኅ የባለሀገር ወታደር ከተማይቱን አጥለቅልቆት አገኘን። የማን ሠራዊት መሆኑን ሲጠይቁ የደጅአዝማች አምባቸው ገሠሠ ጦር መሆኑን እናቴ ሲሰሙ በጣም ደነገጡና እኝህ ሰው የራስ ገብረመድኅን የወንድም የልጅ ልጅ መሆናቸውን ስለሚያውቁ ይህ ልጅ ከተለቀቀ ሄዶ ይናገርና ችግር ይፈጠራል በማለት ተናግረው እንደተያዝሁ በአንድ ክፍል ተዝግቼ አደርሁ። ደጅአዝማች አምባቸው ገሠሠም ወደ ሸዋ በእግር የተጓዘ ስለነበር ሌሊቱን ተነሥተው ተጉዘዋል። እኝህ ሰው አዲስ አበባ ሳይደርሱ ዋድላ አካባቢ ታመው መሞታቸውን ቆይቼ ሰማሁ።