The following is page six of the Amharic text. I have already translated and published up to page 8 (search for Ups and Downs) in the English text, and going forward, after pages seven and eight of the Amharic, I will be finishing the book with simultaneous presentations of the Amharic and the English here on substack. And Godwilling presenting the digital copies on Gumroad and print versions with Amazon. The Amharic original is well-known. I make a few updates of my own, but plan to one day also make the original available. The English is brand spanking new. Hope you are enjoying the story, gursha be’gursha.
አጅሬ ሠፍሮ የነበረው የኢጣሊያው ጦር ሸሽቶ ካመለጠ በኋላ መሬቱም ተራራማ አባጣ ጐባጣ የበዝኀበት በመሆኑ የጠላት ጦር ደፍሮ ለመምጣት ጊዜ ውስዶበታል። ሰፊ ዝግጅት ካደረገ በኋላ ጃኖራን ፣ ቆላ ወገራን ፣ ጠገዴንና በአካባቢው ያሉትን የቆላ ሀገሮች ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ አቅደው ቍጥሩ ከ፲፪ ሺህ በላይ የሚሆን ወታደር ከፍተኛ ዝግጅትና ትጥቅ አስይዘው አንድ ቀን በምሽት ጕዟቸው ወደ ቆላው አደረገ። አርበኛው ወደ ደጋው ጣልያኑ ወደሚገኝበት እየተጓዘ ጥቃት ያደርስ ስለነበረ ፤ የኢጣሊያው ጦር ወደ ቆላው በተጓዘበት ቀን ገብረማርያም ደስታ ፣ በኋላ ፊትአውራሪ ፣ ከሚባል ሰው ቤት ላይ አደጋ ጣለ። ይህ አርበኛ አሥራ ሁለት የጠላት ጦር ገድሎ ሲያመልጥ ጦርነቱ ተጀመረ። ቀንጣ ከሚባለው ሀገር አካባቢ የጠሊማይን ወንዝ ከመያዙ በፊት የጠላት ጦር ባለበት ቦታ ስለተገታ የተኵስ ድምፅ በየአካባቢው ያለውን ሕዝብ ስለቀሰቀሰው ፣ ከርሑቅ ቦታ ያለውም አርበኛ ወሬውን እየሰምዐ ተሰባስቦ የተጧጧፈ ጦርነት ተጀመረ። የጠላት ጦር ውኃ በሌለበት አካባቢ ግጭት በመጀመሩ ትልቅ ችግር ፈጠረባቸው። የውኃው ጥም እያሳበዳቸው ብዙኅ ወታደሮች ዓይናቸውን ጨፍነው በጠላት እጅ ወደተያዘው ወንዝ እየበረሩ በሚመጡበት ጊዜ ለአርበኛው ጥይት ጥሩ ዒላማ ሆነው አለቁ። በዚህ ሁኔታ ፲፪ ቀንና ሌሊት የወሰደ አስከፊ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ ጥቂት የኢጣሊያ ወታደሮች አምልጠው ከመሄዳቸው በስተቀር የተረፈው ከዚያው ተረፍርፎ ቀረ። አርበኛው በዚህ ጦርነት አስደናቂ ድል ከመጐናፀፉ በላይ ቍጥር ሥፍር የሌለው መሣሪያ ለመማረክ በመቻሉ ለሚቀጥለው ውጊያ ሊያሰናዳው ችሏል።
ይህ ጦርነት የተካሄደው እኔና ቤተሰብኤ ከምንኖርበት ቦታ አካባቢ ቅርብ ስለነበር እኛም ከጭንቅ ላይ ወድቀን ሰንብተናል። ሁሉም ሕዝብ በእግዚኦታና በጸሎት ተይዞ ቆይቷል። ከድል በኋላ የወገን ቍስለኛ ወደ ሠፈር ሲመለስ የሞቱት ደግሞ መርዶው ለየቤተሰብአቸው ይደርስ ጀመርና በየመንደሩ ልቅሶው ይሰምዐ ጀመር። እንደማስታውሰው ከዚህ ጦርነት በኋላ የጠላት ጦር ወደ ቆላው ፊቱን ባያዞርም ጀግናው አርበኛ ግን በየምሽጉ እየዘለቀ ይጨፍጭፍ ነበር።
የሀገሬው ሕዝብ ሁሉም ፊቱን ወደ ጦርነቱ ስላዞረ አርበኛውን ለማበረታታት አለቃውን መርጦ የደጅአዝማችነት ማዕረግ ይሰጠውና ተሿሚውም በበኵሉ ሰዎች እየመረጠ ፊትአውራሪ ፣ ቀኝአዝማች ፣ ግራአዝማች ፣ ባዕለአምባራስ እያለ የሹመት ስም እየሰጠ አርበኛው ሁሉ በሹመት በመጥለቅለቁ ፣ የእርሻው ጉዳይ ተዘነጋና መሬት ጦም አዳሪ መሆኗ ሲገርም ጥቂት ሰዎች ያረሱትን አዝመራም አንበጣ ሙጥጥ አድርጐ ስለበላው አርበኛው የሚገኝበት ቆላው ሀገር ከከፍተኛ ረሐብ ላይ ወደቀ። ከላይ በኵል ደጋው ጠላት የሠፈረበት ሲሆን እኛም ያለንበት ሀገር ከእኽል የተራቈተ ስለሆነ መድረሻ ጠፋ። እኛም የዚሁ የአካባቢውን ችግር ተካፋይ በመሆናችን በሕፃንነት ወርኆች ረሐቡንና መከራውን አብረን ተካፈልን። ሕዝቡ ይህ ሁሉ ችግር ገጥሞት ሳለ ለእኛ ማሰቡን ሳያቋርጥ ካለው ዘርም ብትሆን ያካፍሉን ስለነበር ሙቅ ሾርባ እንኳ ከመጠጣት አላቋረጥንም ነበር። ውሎ አድሮ ከማለቅ የሚያድኅነን ነገር ባለመኖሩ የኢጣሊያንን መንግሥት ምሕረት ጠይቀን ወደ ደጋው እንድንመጣና ከዚያም ወደ እናቴ ሀገር ጋይንት እንድንሄድ ተወሰነ። ይህንም እቅድ ከግቡ ለማድረስ የተከተለነው ዘዴ ፊትአውራሪ ደርሶ ኪዳኑ ፣ ኋላ ደጅአዝማች ፣ የሚባሉ ሰው ሽሬ በተደረገው ጦርነት ቈስለው እግራቸው ተሰብሮ ስለነበር ዳባት ላይ የጠላት ጦር ስላገኛቸው ታክመው ሲሻላቸው ለኢጣሊያ ተቀጥረው ከፈረንጁ በታች ትልቅ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ስለነበር ፤ እኝህም ሰው ወይዘሮ ማሚቴ ዘለለው የሚባሉ የእናቴ የአክስታቸው የልጅልጅ በአባቴ በኵል የደጅአዝማች መርሶ ኃይለማርያም የልጅልጅ ቅርብ ዘማዳችንን ያገቡ ስለሆነ በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም ከኢጣልያኑ ምሕረት እንዲያሰጡን መላላክ ተጀምሮ ነበር። የኢጣሊያው ገዢ ቂም የያዘብን የመስለኛል። ፈጥኖ ምሕረት ባይሰጠንም ውሎ አድሮ ስለፈቀደልን እናቴን ፣ እኔንና ወንድሜን ከነበርንበት ቦታ ሸኝተው ድራድራ ከሚባለው ገደል ሥር ዳባት አቅራቢያ አደረሱን።