Editor’s Note:
I have already translated, edited, and published the first eight pages of this book into American (English). They are available here. Once the Amharic text digitization catches up, the Amharic and English will continue being published simultaneously. In the mean time, expect miscellaneous other publications from Aksum Herald in American, as always.
ዳኘው ወልደሥላሴ ረታ እባላለሁ። የተወለድሁት ታኅሣሥ ፳ ቀን ፲፱፻፳ ዓ፡ም በጐንደር ክፍለ ሀገር ወገራ አውራጃ ልዩ ስሙ ዳባት ገብርኤል ከሚባለው ክልል ውስጥ ነው።
የትውልድ ሐረግና እድገት ፡ ከ፲፱፻፳ እስከ ፲፱፻፴፯ ዓ፡ም
ወላጆቼ ቀኝአዝማች ወልደሥላሴ ረታና ወይዘሮ እጅጊቱ ተድላ መኰንን ይባላሉ። ቀኝአዝማች ወልደሥላሴ በአባታቸው ወልቃይት ጠገዴ ፣ ቆላ ወገራ ሲሆኑ ፣ በእናታቸው የሰሜን ተወላጅ ናቸው። የእናታቸው እናት ሀገር ደግሞ ጐጃም ነው። የእናቴ ትውልድ ጐንደር ክፍለ ሀገር ጋይንት ሲሆን አንዱ አያታቸው ደብረታቦር አውራጃ አሞራ ገደል ከሚባለው አካባቢ ተወላጅ ናቸው።
እነዚህ ከሰሜንና ከደቡብ ጐንደር የሚወለዱ ወላጆቼ እኔንና ትንሽ ወንድሜን ደምሴ ወልደሥላሴ ወለዱ።
የወላጆቼን ትውልድ ሐረግ ዘርዘር አድርጌ ለመመዝገብ እወዳለሁ። የአባቴ የቀኝአዝማች ወልደሥላሴ አባት ፊትአውራሪ ረታ ሲሆኑ ፣ እርሳቸውም የጠገዴው ተወላጅ የደጅአዝማች ክንፉ ልጅ ናቸው። እናታቸው ወይዘሮ ኂሩት ጥሶ የቆላ ወገራ ተወላጅ የደጅአዝማች ጥሶ ጐበዜ ትንሽ እኅት ናቸው። ከዚህ ጋብቻ ብዙኅ ልጆች የተወለዱ ሲሆን ማለት አያቴ ፊትአውራሪ ረታ ክንፉ የበኵር ልጅ ናቸው።
የአባቴ እናት ወይዘሮ ጥሩነሽ ገብረመድኅን የሰሜኑ የራስ ገብረመድኅን ኃይለማርያም ልጅ ሲሆኑ ፣ ራስ ገብረመድኅን ኃይለማርያም የወንድሞቻቸውና የኅቶቻቸው ቍጥር ብዙኅ ቢሆንም ለአባታቸው ለደጅአዝማች ኃይለማርያም ገብሬ የበኵር ልጅ ደጅአዝማች ውቤ ኃይለማርያም ሲሆኑ ፣ ኋላም የወረሼኽ ተወላጅ የሆኑትን ወይዘሮ ኂሩት ጉግሣን አግብተው ደጅአዝማች መርሶ ኃይለማርያምን ደጅአዝማች ብጡል ኃይለማርያምንና ወይዘሮ የውብዳር ኃይለማርያምን ወልዷል። ራስ ገብረመድኅን ኃይለማርያም ከሁሉም በእድሜ የሚያንሱ ከመሆናቸውም በላይ በእናታቸው የወገራ ተወላጅ የደጅአዝማች አምሳሌ የልጅ ልጅ በመሆናቸው በሰሜንና በወገራ ሰፊ የዘር ሐረግ አላቸው።
ያርታዒ ጭማሪ:
ኀሠሠ መረመረ ማለት ነው። ታኅሣሥ የምርመራና የመሻት ወቅት ነው።
ውቤ ማለት የሐፄ ቴዎድሮስ ከመንገሡ በፊት የመጨረሻ ምርኮና ኋላ አማች። የልዑል ዓለማየሁ አያት ነው።
ብጡል የእተጌ ጣይቱ አባት ነው።
ኃይለማርያም የሐፄ ሱስንዮስ ዘር ነው ፣ በልጁ ልዕልት መለኮታዊት ፣ የተከታዩ የሐፄ ፋሲል እኅት።።