ዳኘው ወልደሥላሴ ረታ ፲፱፻፹፯ ዓመተ ምሕረት
የአርታዒ አጭር ማሳሰቢያ
የአንድአንድ ልጅና የአንድአንድ ልጅልጅ ቤተሰብእውን የመውደድ ኀላፊነት አለው። ከእነዚህ ብዙኃን ፣ ጥቂቶች የቤተሰብአቸውን ታሪክ ጠባቂና ዘጋቢ የመኾን ተልዕኮ ይኖራቿል። ለእኔ ቤተሰብእ እኔን ከኋለኞቹ ቍጠሩኝ።
ኄኖክ ኤልያስ ነጋሥ
ዳኘው ከኄኖክ ጋር በአሜሪካ ሀገር መጽሐፉ በታተመበት ወቅት
ይህ መጽሐፍ አዘውትረው መልካም ሲመኙልኝና ሲያስበሉኝ ለነበሩት አያቴ ለእማሆይ ጥሩነሽ ገብረመድኅንና አባትና እናት ሆነው በጥንቃቄና በሥነሥርዓት ላሳደጉኝ እናቴ ለወይዘሮ እጅጊቱ ተድላ መታሰቢያ ይሁንልኝ።
የአርታዒ አጭር ማሳሰቢያ
ግራ ያሉት እማሆይ ጥሩነሽ ናቸው። በስተቀኝ ደግሞ ወይዘሮ እጅጊቱ ናቸው።
መግቢያ
በኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜው የተለያዩ መንግሥታት ሥልጣን ይዘዋል። ከእነኝህ መንግሥታት ጐን በመሠለፍ ልዩ ልዩ ተግባር ያከናወኑ ግለሰብእ እንደነበሩ ሁሉ ባንፃሩ ደግሞ የተባሉትን መንግሥታት አቋምና ፖሊሲ (policy) በመቃወም ብዝኁ የተሰቃዩና የተገደሉም ነበሩ ፣ አሁንም አሉ ፣ ለወደፊትም ይኖራሉ።
የግለሰብእ ታሪክ የአንድ አገር ታሪክ ሊሆን አይችልም። ሆኖም ግለሰብእ በሕይወት የደረሰባቸው ውጣ ውረድ የተጫወቱት ሚና ያበረከቱት አስትዋጽዖ ወዘተ ተደማምሮ በትክክል ሲቀርብ የአንድን አገር ታሪክ ለመጽሐፍ ለሚፈልጉ ሞያተኞች ምሁራን በምንጭነት በኩል ዓይነተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል። ሕዝብም ከድርጊታቸው ከእምነታቸውና ከስቃያቸው ብቻ ሳይሆን ከሽተታቸውም ብዝኁ ነገር ለመምሃር ይቻላል።
አቶ ዳኘው ወልደሥላሴ ቀደም ሲል የእስራት ዘመን በአበሻ አገር እንዲሁም የአድዋ ዘመቻና የአፄ ምኒልክ አነሣስ የተሰኙትን ሁለት በውጭ አገር ቋንቋ የተጸሐፈ መጽሐፍት ወደ ዐምሐርኛ ተርጕመው ለአንባቢያን ማቅረባቸው የሚታወስ ነው። ይህም ድርጊት ልምርምር ለጥናትና ለታሪክ ያላቸውን ዝንባሌ ይጠቁማል።
አሁን ደግሞ ውጣ ውረድ የበዝኀበት ሕይወት በሚል ርዕስ የግል የሕይወት ታሪካቸውን ጽሕፈዋል። የአስተዳደግ አከባቢያቸው ምን ይመስል እንደነበር የኢጣልያ ፋሽስት (fascist) ወታደር ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የደረሰባቸው ችግር ዘመናዊ ትምህርት እንዴት ለመቀሠም እንደቻሉና ከጐንደር ወደ አዲስ አበባ ሄደው በወቅቱ የመምህራን ማሠልጠኛ ኰለጅ ይባል በነበረው ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ተመርቀው በልዩ ልዩ ዘርፎች የትምህርት ሚኒስቴር (minister) ተዛውረው ፣ በግብፅ ፣ በቫቲካን ፣ በከሰላ ፣ በሳውዲ አረቢያና በመጨረሻም በአምባሳደርነት ማዕረግ በሰሜን የመን ኋላም የጐንደር ክፍለሀገር ዋና አስተዳዳሪ ሆነው እንዴት እንደተሾሙና ሽአለቃ መልአኩ ተፈራ የሚባለው የደርግ አባል አፍኖ ወስዶ ሊረሽናቸው ሲል እንዴት እንደተረፉ አብራርተው ጽሕፈዋል።
ውጣ ውረድ የበዝኀበት ሕይወት በአጽሐጽሐፉ ፣ በአቀራረቡ ፣ በቋንቋ ጥራቱና በታሪክነቱ ተነባቢ ሲሆን ፤ ሌሎችንም ኢትዮጵያውያን የግል ሕይወት ታሪካቸውን ጽሕፈው ለአንባቢያን እንዲያበረክቱ የምያደፋፈር ነው።
ቀኝአዝማች ሣህሌ አዩ